የአንበጣ መንጋውን የመከላከሉ ስራ በአውሮፕላን እጥረት ችግር ገጥሞታል - የግብርና ሚኒስቴር

61

አዲስ አበባ መስከረም 27/2013 በኢትዮጵያ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ የመከላከሉ ጥረት በአውሮፕላን እጥረት ችግር እንደገጠመው የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ። 

ሚኒስቴሩ በአገሪቷ የበረሃ አንበጣ የመከላከል ሂደት ያለበትን ደረጃና ቀጣይ እርምጃዎች አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

የበረሃ አንበጣ በቀን ከ50 እስከ 100 ኪሎ ሜትር በፍጥነት የሚጓዝ ሲሆን ሰብል የማውደም አቅሙም ከፍተኛ ነው።    

የሚኒስቴሩ መረጃ እንደሚያመለክተው እስካሁን በ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ አሰሳ የተደረገ ሲሆን ግማሽ ሚሊዮን ሄክታር ላይ በተለያዩ መንገዶች የመከካከል ስራ ተሰርቷል።   

በኀብረተሰብ ተሳትፎ፣ በመኪናና በአውሮፕላን በመታገዝ የኬሚካል ርጭት መደረጉን ነው ሚኒስቴሩ የገለፀው።   

ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ማንደፍሮህ ንጉሴ እንደገለጹት፤ በእስካሁኑ የመከላከል ሂደት በደቡብ ክልል ኮንሶና አርባ ምንጭ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ቦረናና ጉጂ አንበጣውን ማጥፋት ተችሎ ነበር።     

ይሁንና በአማራና አፋር ክልሎች ድንበሮች ላይ የመከላከል ስራ እየተከናወነ አንበጣው ከየመን፣ ጅቡቲና ሱማሌ ላንድ በድጋሚ መግባቱ ጫና መፍጠሩን ነው የተናገሩት።    

እስከ መጪው ታህሳስ መጨረሻ የአንበጣው መንጋ እንደሚገባ የሚጠበቅ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ የምርት ወቅት በመሆኑ ትልቅ ተጽዕኖ ሊያመጣ ስለሚችል ጠንካራ ስራ ይጠበቃል ነው ያሉት።    

የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል በሚኒስትር ዴኤታዎች የሚመራ አደረጃጀት መፈጠሩንና በዚህም እስከ ቀበሌ ድረስ ባለሙያዎችን ባሳተፈ መልኩ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሆነም ገልፀዋል።

የአንበጣ መንጋውን ለመቆጣጠር 10 አውሮፕላኖች እንደሚያስፈልጉ የገለጹት ዶክተር ማንደፍሮህ  በብልሽትና በአደጋ ምክንያት እየሰራ ያለው አንድ አውሮፕላን ብቻ እንደሆነ ነው ያስረዱት።

የአውሮፕላን እጥረቱን ለማቃለል ከሱዳን ግብርና ሚኒስቴር ሁለት አውሮፕላኖች ለማግኘት ጥረት እየተደረገና ከባለሃብቶች በኪራይ በማምጣት የኬሚካል ርጭቱን ለማካሄድ እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።      

በዓለም አቀፉ የምግብና እርሻ ድርጅት በኩል ተጨማሪ ሁለት አውሮፕላኖች ለማግኘት ሁኔታዎች እየተመቻቹ መሆኑንም ጠቁመዋል።

እንደ ዶክተር ማንደፍሮህ ገለፃ 112 ተሽከርካሪዎች ኬሚካል መርጫ መሳሪያ ተገጥሞላቸው ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን ቁጥጥሩን ለማጠናከር ሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶች ሁለት ሁለት ተሽከርካሪዎችን በነፍስ ወከፍ እንዲያቀርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አቅጣጫ ተቀምጧል።

የኅብረተሰብ ተሳትፎ ወጥነት የሌለው መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ማንደፍሮህ ማኅበረሰቡ ማንንም ሳይጠብቅ በራሱ የመከላከል ስራውን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም