አገራት የበረራ ክልከላ የሚያደርጉባቸው አካባቢዎች እንዳሉ ሁሉ በኢትዮጵያም ተመሳሳይ አሰራር አለ-- የሲቪል አቬየሽን ባለስልጣን

112

አዲስ አበባ መስከረም 27/2013 (ኢዜአ) ሀገራት የአየር በረራ ክልከላ የሚያደርጉባቸው የተመረጡ አካባቢዎች እንዳሉ ሁሉ ኢትዮጵያም የከለከለችባቸው ቦታዎች መኖራቸውን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን ገለጸ።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት በርካታ አገራት ምንጊዜም የበረራ ክልከላ የሚያደርጉባቸው የተመረጡ አካባቢዎች አሉ።

በዓለም አቀፍ የአቪየሽን ዘርፉ የተለመደና የታወቀ አሰራር መሆኑን ጠቅሰው በርካታ ሀገራት በተለይ ሃብቶቻቸው ያሉባቸውን አካባቢዎች የአየር በረራ እንዳይካሄድባቸው ያደርጋሉ ብለዋል።

በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያም የአየር በረራ እንዳይካሄድ የከለከለቻቸው የተመረጡ አካባቢዎች መኖራቸውን ኮሎኔል ወሰንየለህ ገልጸዋል።

ሌሎች ለበረራ የተከለከሉ አካባቢዎች እንዳሉ ሆነው የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም በረራ የማይደረግበት የተከለከለ ስፍራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ግድቡ የሀገሪቷ ትልቅና መጠበቅ ያለበት ሃብት በመሆኑ ባለስልጣኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር የአየር በረራ ክልከላ አድርጓል ብለዋል።

እንደ ኮሎኔል ወሰንየለህ ገለጻ ማንኛውም ሀገር የአየር ክልከላ ያደረገባቸውን አካባቢዎች ለሁሉም የዓለም ሀገራት ማሳወቅ ይጠበቅበታል።

ኢትዮጵያም ይህንኑ ያደረገች ሲሆን በዓለም በአቪየሽን ዘርፉ የተለመደ አሰራር ስለመሆኑም ገልጸዋል።

ሀገራት በአየር ክልላቸው በረራ እንዳይካሄድ በሚከለክሏቸው የተመረጡ አካባቢዎች ምንም አይነት ተጽዕኖ ሊደርስባቸው እንደማይችልም አብራርተዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አሁን ላይ 75 በመቶ የደረሰ ሲሆን ሁለቱ ተርባይኖች በተያዘው ዓመት ሃይል ማመንጨት ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም