ኮሮና መከላከልን ታሳቢ በሚያደርገው የትምህርት ሥራ የዘርፉ ባለሙያዎች ግንባር ቀደም ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

68

ባሕርዳር፣ መስከረም 26/2013 (ኢዜአ) በ2013 ትምህርት ዘመን በሚካሄደው ኮሮና መከላከልን ታሳቢ ያደረገ የመማር ማስተማር ሥራ የትምህርት ባለሙያዎች ግንባር ቀደም ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አስገነዘቡ።

በክልሉ በ2013 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራ ለመጀመር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የመከረ መድረክ በባሕርዳር ተካሂዷል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ በወቅቱ እንደገለጹት የኮሮና ቫይረስ ክስተት በትምህርት ዘርፉ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል።

"ተፅዕኖውም የትውልድ ክፍተትን ሊፈጥር የሚችል ፈተና ነው" ብለዋል።

በ2013 የትምህርት ዘመን ኮሮና መከላከልን ታሳቢ ያደረገ የመማር ማስተማር ሥራ በማካሄድ ትውልድን ለማሻገር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የኮሮና ቫይረስ ተፅዕኖ በመቋቋም ትውልድን ለማሻገር በሚከናወነው የመማር ማስተማር ሂደት የትምህርት ባለሙያዎች ግንባር ቀደም ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አስገንዘበዋል።

በየደረጃው ያለው አመራር፣ ወላጆችና ኅብረተሰቡን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት፣ የዘንድሮው የትምህርት ሥራ በታለመለት መልኩ እንዲከናወን የድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።

የክልሉ መንግሥት የመማር ማስተማር ሥራው በተሳካ ሁኔታ እንዲቀጥል አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ አስታውቀዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው በክልሉ በሚገኙ  ትምህርት ቤቶች ኮሮና መከላከልን ታሳቢ ያደረገ  የመማር ማስተማር ሥራ ለመጀመር ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በወረዳና ከዚያ በታች ባሉ ትምህርት ቤቶች ጥቅምት 9 እንዲሁም  በዋና ከተሞች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም የመማር ማስተማር ሥራ እንደሚጀመር አመላክተዋል።

በክልሉ 60 በመቶ በሚሆኑ ትምህርት ቤቶች በሁለት ፈረቃና  በ25 በመቶዎቹ በሦስት ፈረቃ ትምህርት እንደሚሰጥ ጠቅሰዋል።

የተማሪ ቁጥር ከፍተኛ በሆነባቸው ቀሪ ትምህርት ቤቶች ደግሞ ቅዳሜና እሁድን ጨምሮ በአራት ፈረቃ ትምህርት ለመስጠት አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል።

በትምህርት ቤቶች የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ግብዓቶች እጥረትና የክፍል ጥበት ሥጋቶችን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በትምህርት ቤቶች የተማሪዎችን ርቀት ለመጠበቅ ኅብረተሰቡን በማስተባበር ከአምስት ሺህ በላይ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ተገንብተው ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸውን የቢሮው ኃላፊ አስታውቀዋል።

"ትምህርት ቤቶች ተከፍተው የመማር ማስተማር ሥራውን መጀመር ግድ ነው" ያሉት ደግሞ የክልሉ መምህራን ማኅበር ምክትል ሊቀመንበር አቶ አደበ አቻምየለህ ናቸው።

ትምህርት ቤቶች ሲከፈቱ  ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ማሟላት አስፈላጊ መሆኑን ምክትል ሊቀ መንበሩ አስገንዝበዋል።

በምክክር መድረኩ የክልልና  የዞን ጤና፣ ትምህርትና ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች መምሪያ ኃላፊዎችን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻዎች ተሳትፈዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም