ብሄራዊ መግባባትን በማጠናከር አገሪቱን ወደ ከፍታ ለማውጣት በሚደረገው ጥረት ሁሉም ሊተጋ ይገባል- መንግስት

173
አዲስ አበባ ግንቦት 3/2010 ካለፉት ስኬቶችና ድክመቶች የተገኙ ተሞክሮዎችን መሰረት በማድረግ የተፈጠረውን ብሄራዊ መግባባት በማጠናከር፣ የህዳሴ ጉዞውን ለማስቀጠልና አገሪቱን ወደ ከፍታ ለማውጣት ሁሉም ዜጋ በተሰማራበት ዘርፍ ለውጤት እንዲተጋ መንግስት ጥሪ አቀረበ። የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው ሳምንታዊ የአቋም መግለጫ፤ ብሄራዊ መግባባትን በማጠናከር አገሪቱን ወደ ከፍታ ለማውጣት በሚደረገው ጥረት ሁሉም ዜጋ ሊረባረብ እንደሚገባ አፅኖኦት ሰጥቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ከሰሞኑ በጅቡቲ፣ በሱዳንና በኬንያ ባካሄዷቸው የሥራ ጉብኝቶች ከአገሮቹ ጋር የጠበቀ ግንኙነትንና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብቱ ልዩ ልዩ ስምምነቶች መፈራረማቸውን መግለጫው አመላክቷል። ኢትዮጵያ የጅቡቲን ወደብ በጋራ በማልማት ተጠቃሚ እንድትሆን፣ በሱዳኑ የፖርት ሱዳን ወደብም ኢትዮጵያ ብቻ የምትጠቀምበትን ወደብ በጋራ ለማልማትና ለማስተዳደር፣ አገሮቹን በመሰረተ ልማት ለማስተሳሰር ስምምነት ላይ መደረሱን መግለጫው አመላክቷል። በአገሮቹ በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንዲለቀቁ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡትን ጥሪ በመቀበል እስካሁን ሱዳን ከ1ሺህ400 በላይ ወገኖችን ከእስር መልቀቋን ያመላከተው መግለጫው ይህም ከጉብኝቱ ውጤቶች መካከል አንዱ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባ ጠቁሟል። የአገራዊ ደህንነትና የውጭ ግንኙነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ሰነድ ከጎረቤት አገሮች ጋር እንደቀድሞው ዘመን በጥርጣሬና በጠላትነት ከመተያየት አላቆ በእኩልነት እና በጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ በጋራ መስራት ማስቻሉን መግለጫው አትቷል። ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ መድረክ ያላት ተሰሚነትና መልካም ገጽታ ተጠናክሮ የቀጠለው ውስጣዊ ተጋላጭነቱን በሚቀንሱና ውስጣዊ ጥንካሬን በሚያጎለብቱ ጉዳዮች ላይ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ መሆኑም በመግለጫው ተመልክቷል። የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ተቀምጧል። በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ ግንቦት 03 ቀን 2010 . ብሄራዊ መግባባትን በማጠናከር አገራችንን ወደ ከፍታ ለማውጣት ሁሉም ሊተጋ ይገባል ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ሰሞኑን በጅቡቲ፣ በሱዳንና በኬንያ ባካሄዷቸው የሥራ ጉብኝቶች ከአገራቱ ጋር የጠበቀ ግንኙነትንና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብቱ ልዩ ልዩ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል፡፡ ኢትዮጵያ የጅቡቲን ወደብ በጋራ በማልማት ተጠቃሚ እንድትሆን፣ በሱዳኑ የፖርት ሱዳን ወደብም ላይ ኢትዮጵያ ብቻ የምትጠቀምበትን ወደብ በጋራ ለማልማትና ለማስተዳደር፣ አገራቱን በመሰረተ ልማት ለማስተሳሰር እና የመሳሰሉ አካባቢያዊና አህጉራዊ ጠቀሜታ ያላቸው ስምምነቶች ተደርሰዋል። የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱም ይበልጥ እንዲጠናከር መግባባት ላይ የተደረሰ ሲሆን በነዚህ አገራት በእስር ላይ የሚገኙ ኢተዮጵያውያን እንዲለቀቁ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡትን ጥሪ በመቀበል እስካሁን ሱዳን ከ1ሺህ 400 በላይ ወገኖቻችንን ከእስር ለቃለች። ይህም ከጉብኚቱ ውጤቶች መካከል አንዱ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። አገራችን ኢትዮጵያ የምትገኘው የተለያዩ ፍላጎቶችን እያስተናገደች ባለችው ዓለማችን ውስጥ ትርምስና ቀውስ ተለይቶት በማያውቀው የአፍሪካ ቀንድ ነው፡፡ አገራችን የራሷን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ እና ልማቷን ለማስቀጠል ቀጠናው አዳጋች መስሎ ቢታይም ከግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ወዲህ በተከተልነው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲና ስትራቴጂ መሰረት የራሳችንን ሰላምና ልማት አስተማማኝና ቀጣይ ከማድረግ ባለፈ ለአካባቢያዊ ሰላምና ብልዕግና ግንባር ቀደም ተዋናይ ሆነን መስራት ችለናል። በተለይም በተሃድሶው ማግስት በወጣው የአገራዊ ደህንነትና የውጭ ግንኙነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ሰነድ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው ከጎረቤት አገሮች ጋር እንደቀድሞው ዘመን በጥርጣሬና በጠላትነት ከመተያየት ተላቀን በእኩልነት እና በጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ እንድንሰራ አስችሎናል። ለውጫዊ ጥንካሬያችን መሰረቱ በአገር ውስጥ የምንሰራው ሥራ መሆኑ ታምኖበት ውስጣዊ ተጋላጭነትን በመቀነስ እና ጥንካሬያችንን በማጎልበት ላይ አተኩረን በመስራታችን ቀደም ባለው ጊዜ ድርቅና የእርስ በርስ ጦርነት፣ ድህነትና ኋላቀርነት የአገራችን የዘላለም እጣ ፋንታ ይመስል የነበረው መጥፎ ገጽታ በአወንታዊ መልኩ ተቀይሯል። የውስጥ ችግሮቻችንን ከመፍታት አንጻር የጎረቤት አገራትን ሚና ተገንዝበን ለእኩልነት እና ለጋራ ተጠቃሚነት በመስራታችን ዛሬ ከኤርትራ በስተቀር ከሁሉም የቀጠናው አገሮችና መንግስታት ጋር በመልካም ጉርብትና ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ፈጥረን ለጋራ ተጠቃሚነት በርትተን በመስራታችን ከጎረቤቶቻችን ጋር ያለን ግንኙነት ከመቸውም ጊዜ በላይ በእኩልነትና ወንድማማችነት ትብብር መንፈስ ላይ የተገነባ በመሆን ላይ ይገኛል፡፡ ውስጣዊ አቅማችንን በማጠናከር ላይ ሙሉ ትኩረታችን አድርገን በሰራነው ሥራ ዛሬ አገራችን በቀጠናው ብቻ ሳይሆን በታላላቅ ዓለም አቀፋዊ መድረኮች ጭምር ተሰሚነት ያላት፣ በድህነትና ኋላቀርነት ሳይሆን በፈጣን እድገትና ድርቅን በመቋቋም አቅሟ፣ በእርስ በርስ ጦርነትና ግጭት ሳይሆን በኮንፈረንስ ማዕከልነቷ፣ በኢንቨስትመንት፣ ንግድና ቱሪዝም መስህብነቷ የምትታወቅ አገር መሆን ችላለች፡፡ አገራችን በዓለም አቀፉ መድረክ ያላት ተሰሚነትና መልካም ገጽታ ተጠናክሮ የቀጠለው ውስጣዊ ተጋላጭነታችንን በሚቀንሱ እና ውስጣዊ ጥንካሬያችንን በሚያጎለብቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተን በመስራታችን ነው፡፡ ይሄው ሁኔታ ወደፊትም ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል። በመሆኑም አሁን የተፈጠረውን ብሄራዊ መግባባት በማጠናከር፣ ካለፉት ስኬቶቻችንና ድክመቶቻችን ያገኘነውን ተሞክሮ መሰረት በማድረግ ህዳሴያችንን ለማስቀጠል እና አገራችንን ወደ ከፍታ ለማውጣት ሁሉም ዜጋ በተሰማራበት ዘርፍ ለውጤት እንዲተጋ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም