የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ለዶክተር አደም ሂኮ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጠ

93

ሐረር፣ መስከረም 22/2013 (ኢዜአ) የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ለዶክተር አደም ሂኮ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ መስጠቱን አስታወቀ::

የዩኒቨርሲቲው የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሮክቶሬት ዳይሪክተር አቶ አለም እሸት ተሾመ ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ለዶክተሩ ሙሉ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ የሰጠው በባዮ- ሜዲካል ሳይንስ የምግብ ደህንነትና ዙኖሲስ ዘርፍ ነው።

"በመማር ማስተማር፣ በምርምር ስራዎቻቸውና በማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ላበረከቱት የላቀ አፈፃፀም ዩኒቨርሲቲው የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ እንዲያገኙ አድጓል" ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ መስከረም 20 ቀን 2013 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ገምግሞ ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ በመቀበል ለዶክተሩ ማእረጉ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።

ዶክተር አደም ሂኮ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ በሆኑ የምርምር ጆርናሎች ላይ 42 ፅሁፎችን ማውጣታቸውን አስታውሰዋል።

ለሁለተኛ ዲግሪ የምርምር ስራ የሰሩ 16 ተማሪዎችን እንዲሁም ከ20 በላይ ለሆኑ የእንስሳት ህክምና ተመራቂ ዶክተሮች አማካሪ በመሆንም ሰርተዋል፡፡

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ እንስሳት ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ የምርምር አስተባባሪ፣ የኮሌጁ ዲን፣ የኢስት አፍሪካን ጆርናል ኦፍ ሳይንስ ኤዲቶሪል ማናጀር፣ የመማር ማስተማርና ማህበረሰብ አገልግሎት የስራ ዘርፍ ኃላፉ ሆነው ማገልጋቸውን ተናግረዋል ።

በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ከ10 ዓመታት በላይ ያገለገሉ፣ በየጊዜው የትምህርት ዝግጅታቸውን በማሻሻል የረዳትና የተባባሪ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ያገኙና በሁለት የእውቀት ዘርፍ ባለሁለት ዶክትሬት ዲግሪ ባለቤት መሆናቸውን ዳትሬክተሩ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም