የአማራ የአመራር አካዳሚ ወደ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ሊያድግ ነው

66

ባህርዳር መስከረም 21/2013 (ኢዜአ) የአማራ አመራር አካዳሚ የተሻለ ብቃት ያላቸውን አመራሮችን በዘላቂነት ለማፍራት ወደ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ለማደግ የሚያስችለውን ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቁ። 

የአካዳሚው ፕሬዚዳንት ዶክተር ማተቤ ታፈረ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት አካዳሚውን ወደ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ማሳደጉ ተተኪ አመራሮችን በዘላቂነት ለማፍራት ነው።

አካዳሚው የክልሉንና የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ተረድቶ መፍትሄ የሚሰጥ አመራር በማፍራት አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ መቆየቱን አውስተዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በፖለቲካል ኢኮኖሚ፣ በፐብሊክ ፖሊሲና ሊደርሽፕና ሌሎችም የትምህርት መስኮች በሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ መሆኑን ገልፀዋል።

አካዳሚው ወደ ስቴት ዩኒቨርስቲ ማደጉም ቀደም ሲል የጀመረውን የማስተማር ስራ ወደ ተሻለ ደረጃ በማብቃት ከክልሉ አልፎ ለሀገር ብቁ የሆኑና  መጪውን ጊዜ መተንበይ የሚችሉ ብቃት ያላቸውን አመራሮችን በብዛት ለማፍራት እንደሚያስችለው ተናግረዋል።

በስሩም የፖሊሲና ስትራቴጂክ፣ የመፍትሄና የሃሳብ አመንጪ ማዕከላትን ለመገንባት፣ የስልጠናና የብቃት ማረጋገጫ፣ የምርምርና ህትመንት ሴንተሮችም እንዲኖሩት ይደረጋል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም ለአንድ ሺህ 200 ተማሪዎች ማደሪያ የሚሆን ባለአራት ወለል ህንፃ እየተገነባ መሆኑን አመልክተው 50 የመማሪያ ክፍሎች ያላቸው አራት ህንፃዎች ግንባታም በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋልል።

በአካዳሚው የተቀረፁት የትምህርት መስኮችም በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች በአብዛኛው የማይሰጡና የአመራር ብቃትን ለማሳደግ ተመርጠው የሚሰጡ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ለዚህም ለመማር ማስተማር ስራው የሚያስፈልጉ መምህራን፣ መፃህፍትና ሌሎች ግብዓቶችም ቀደም ሲል እንዲሟሉ መደረጉን አስታውቀዋል።

አካዳሚው የስቴት ዩኒቨርሲቲ የማስተማር ስራውንም በቅርቡ የክልሉ ምክር ቤት በሚሰጠው ውሳኔ መሰረት ወደ ማስተማር ስራ ይገባል ብለዋል።

አካዳሚው ዘንድሮ ን 200 ተማሪዎችን በማታውና  መደበኛው የትምህርት መርሃ ግብር በሁለተኛ ዲግሪ ተቀብሎ ለማስተማር ምዝገባ እያካሄደ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም