የኦሮሚያ ፖሊስ የኢሬቻ በዓልን ሊያውኩ ነበር ያላቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገለጸ

101

መስከረም 21/2013 ( ኢዜአ)  የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የኢሬቻ በዓልን ለማወክ ሲንቀሳቀሱ ነበር ያላቸውን 503 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ መርዳሳ እንዳሉት "የኢሬቻ በዓል በሰላም እንዳይከበር ለማወክ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል"።

በተጨማሪም 14 ክላሽንኮቭ መሳሪያ፣ 26 ቦምብ፣ 103 ሽጉጦች ፖሊስ ባደረገው ፍተሻ መያዛቸውን አስታውቀዋል።

ህብረተሰቡ ክልሉን የሁከትና የብጥብጥ አውድማ ለማድረግ የሚንቀሰቀሱ ቡድኖችን ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ሊመክታቸው ይገባል ብለዋል።

በአዲስ አበባና በቢሾፍቱ የሚከበረውን የኢሬቻ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ፖሊስ ዝግጅት ማድረጉንም አስታውቀዋል።

 ህብረተሰቡም ከፖሊስ ጎን በመሆን ሰላሙን እንዲጠብቅ ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ መርዳሳ አሳስበዋል።
 
በዓሉ አባገዳዎች ባስቀመጡት መመሪያ እንዲከበር፣ ህብረተሰቡም ይህን በመረዳት የኮሮና ቫይረስን መከላከልን መሰረት ባደረገ መልኩ መንቀሳቀስ እንዳለበት ጠቁመው ፖሊስም ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ፖሊስ ከመስከረም በኋላ መንግስት የለም በማለት ህዝብን የሚያውኩ ግለሰቦችና ቡድኖችን አይታገስም ያሉት ኮሚሽነር ጄኔራሉ ከምንጊዜውም በላይ የህግ የበላይነትን ለማስከበር ይሰራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም