አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ማዕከል ከአምስት ተቋማት ጋር የመግባቢያ ስምምነቶች ተፈራረመ

119

አዲስ አበባ፣ መስከረም 21/2013 ( ኢዜአ) አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ማዕከል ከአምስት ተቋማት ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችሉትን የመግባቢያ ስምምነቶች ዛሬ ተፈራረመ፡፡

ከማዕከሉ ጋር  ለመስራት ስምምነቶቹን የፈረሙት ዘውዲቱ ሆስፒታል፣አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ፣አዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩትና የኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ ናቸው፡፡

ስምምነቶቹ በፋይናንስ ፣በትምህርትና በጤና ዘርፎች በጋራ ለመስራት እንደሚያስችሉ ተገልጿል፡፡

አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ማሽኖች ሰው ሰራሽ የሆነ የማሰብ ክህሎትን በመጠቀም የሰው ልጅን በማገዝ በተለያዩ መስኮች እንዲሰማሩ የሚደረግበት ሳይንሳዊ አሰራር ነው።

በጤና፣ በግብርና፣ በትራንስፖርት፣ በሕዝብ ጥበቃና ደህንነትና በሌሎችም ዘርፎች ጥቅም ላይ በማዋል ለአገር ብልጽግና የሚረዱ የምርምር ውጤቶች ለማፍለቅ እየተሰራ መሆኑም ተመልክቷል።

የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት እንደገለጹት ማዕከሉ ከተመሰረተ አጭር ጊዜ ቢሆነውም፤ዓላማዎቹን ለማሳካት ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ ነው።

በአርቴሻል ኢንተለጀንስ የልህቀት ማዕከል ለመሆን መሰረተ ልማትን ጨምሮ በዘርፉ ራሱን የቻለ ፖሊሲ እንዲኖር ዓላማን አንግቦ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም ስኬት ከመንግሥትና ከግል ተቋማት ጋር በጋራ ይሰራል ብለዋል።

ስምምነቶቹ የዚሁ አንድ አካል መሆኑን  ያመለከቱት ኢንጂነር ወርቁ፤ በቀጣይ ሌሎች ተቋማትም ከተቋሙ ጋር በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ስምምነቶቹን የተፈራራሙት ተቋማት ኃላፊዎች በበኩላቸው የመግባቢያ ሰነዱ በየዘርፋቸው ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ገልጸዋል።

የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ ኤጀንሲው አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ ከአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ማዕከል ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን እንሰራለን ብለዋል።

የኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ደርቤ ተሾመ ከማዕከሉ ጋር ለመስራት ቁርጠኞች መሆናቸውንና በየትኛው ዘርፍ ተባብረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል። 

በማዕከሉ በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ ተቋማት ጋር የምርምር ሥራዎች እያከናወነ መሆኑ ተነግሯል።

በተለይ በጡት ካንሰር፣ በኢንተለጀንስ የትራንስፖርት ሥርዓት፣ በፋይናንስና በግብርና ዘርፎች የሚካሄዱት ምርምሮች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውም ተገልጿል።

ማዕከሉ ለውጥ የሚያመጡና ወደ ተግባር የሚለወጡ ቴክኖሎጂዎች በተቀናጀ መልኩ ለማፍለቅ መቋቋሙ በቅርቡ ምረቃው በተካሄደበት ሥነ ሥርዓት ላይ መገለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም