ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎች የሚሰለጥኑበት የሥርዓተ ትምህርት ቀረፃ እየተጠናቀቀ ነው- ሚኒስቴሩ

74

አዲስ አበባ፣ መስከረም 21/2013 ( ኢዜአ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎች የሚሰለጥኑበት ሥርዓተ ትምህርት ቀረፃ እያጠናቀቀ መሆኑን ገለጸ።

ሚኒስቴሩ የልዩ ተሰጥኦ/ታለንት/ ልማት ኢንስቲትዩት ለመክፈት የመሰረተ ልማት ተቋማት ግንባታና የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት እያጠናቀቀ መሆኑን ገልጿል።

ኢንስቲትዩቱን ሥራ ለማስጀመር በተቀረፀው ሥርዓተ ትምህርት ላይ የመጨረሻ ግብዓት የሚያሰባስብበት ዛሬ ውይይት አድርጓል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሲሳይ ቶላ በመድረኩ ላይ እንዳሉት ኢንስቲትዩቱ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ወጣቶችና ጎልማሶችን ተቀብሎ ማሰልጠን ይጀምራል።

ኢንስቲትዩቱ የሚቀበላቸው የስምንተኛ ክፍል ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ዘጠነኛ ክፍል የተዛወሩ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎች እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

ስልጠናው ከመደበኛ ትምህርታቸው ጎን ለጎን ልዩ ተሰጥኦዋቸውን የሚያበለጽጉበት እንደሚሆንም አቶ ሲሳይ አስረድተዋል።

በተጨማሪም የልዩ ተሰጥኦ ባለቤት ሆነው መደበኛ ትምህርት ያልወሰዱ ጎልማሶችም ተሰጥኦቸውን የሚያሳድጉበት ስልጠና እንደሚከታተሉም ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ አንድ ሺህ ተማሪዎች ተቀብሎ ሥራ እንደሚጀምር ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል።

ስልጠናው በመደበኛና መደበኛ ያልሆነ ሥርዓትን ተከትሎ ዘርፉን ለማሳደግና ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።

የኢንስቲትዩቱ የሥርዓተ ትምህርት ፕሮጀክት ማናጀር ዶክተር ሒርጳሳ ጫላ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ መሰረታዊ የሚባለውን የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትና የመሰረተ ልማት ተቋማት ግንባታ እያጠናቀቀ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ከሥርዓተ ትምህርት ቀረፃው ጎን ለጎን የተማሪዎችና የመምህራን ምልመላ መስፈርት  ማዘጋጀቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም