የምስጋና በዓል በሆነው ኢሬቻ ላይ የአባገዳዎችን ምክር መተግበር ይገባል ...በኦሮሚያ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች

192

መስከረም 21/2013 (ኢዜአ) የበዓሉ ታዳሚ በዓሉን በሰላም አክብሮ እንዲመለስ በአባ ገዳዎች የተቀመጡ ምክሮች እንዲከበሩ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት ሲሉ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪ አቀረቡ። 

የፓርቲዎቹ አመራሮች የዘንድሮውን የኢሬቻ በዓል አከባበር አስመልክተው ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

የጤና ባለሙያዎችን ጥንቃቄ ተግባራዊ በማድረግ "ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስንተርፍ በነቂስ ወጥተን በዓላችንን እናከብራለን" ያሉት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው፤ ለዚህም የጸረ ሰላም ኃይሎችን ጥሪ ወደ ጎን በማለት ታላቁን በዓላችንን ከወከባና ከረብሻ መጠበቅ አለብን ብለዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ንቅናቄ ሊቀ መንበር እና የኢትዮጵያ ፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረት ሰብሳቢ አቶ ደረጀ በቀለ እንዳሉት በዓሉ የምስጋና በዓል ነው፤ በዚህ በምስጋና ቀን ደግሞ ፈጣሪን ማመስገን እንጂ ፖለቲካና ተቃውሞ ማራመድ አይገባም" ብለዋል።

"የኮቪድ ወረርሽኝ ጊዜያዊ ክስተት ነው" ያሉት የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ ሊቀመንበር አቶ ቶለሳ ተስፋዬ በበኩላቸው "ኮሮና በግለሰቦች ወይም በመንግስት ፍላጎት ሳይሆን ለዓለም የመጣ ወራሪ በሽታ ነው" ብለዋል።

"በዚህ ጥንቃቄ በሚያሻው ጊዜ እንደ ፖለቲካ ፓርቲዎች የህዝባችን በሰላም ወጥቶ መግባት ያሳስበናል" ያሉት አቶ ቶሎሳ፤ የኢሬቻ በዓልን ለፖለቲካና ለሌላ ዓላማ መጠቀሚያ መድረግ ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ሰለሞን ታፈሰ በበኩላቸው "የኦሮሞ ህዝብ ባህልና ክብሩን የሚያውቅ በአባ ገዳዎች የሚመራ ጨዋ ህዝብ በመሆኑ ከውጭና ከውስጥ ጥሪ አድርገው ባህሉን የሚያደፈርሱትን አካላት መከላከል አለበት" ብለዋል።

ሁኔታው የህይወት ጉዳይ ነው የሚሉት አቶ ሰለሞን፣ በኮቪድ ምክንያት አባ ገዳዎች የዚህን ዓይነቱን የአከባበር መመሪያ ማስቀመጣቸው ለህዝባቸው ማሰባቸውን አመላካች ነው ብለዋል።

የመላ ኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ ተሰማ ሁንዱማ በበኩላቸው በዓሉ የኦሮሞ እና የመላው የኢትዮጵያ ህዝብ በዓል በመሆኑ ሳይረበሽና ሳይደፈርስ በደስታ እንዲከበር አሳስበዋል።

"መላው ህዝባችን በተለይም ስለ ኮቪድ ግንዛቤ ያለው ማንም አካል የኮቪድን አደገኛነት ተረድቶ በዓሉን በቤቱ ሆኖ እንደሚያከብር ሙሉ እምነት አለን" ብለዋል።

ዓመቱ የሰላም፣ የደስታና የጥሩ ስራ ዘመን ይሁንልን ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ፤የእንኳን ለምስጋና በዓል ለእሬቻ በሰላም አደረሳችሁ መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም