በደቡብ ክልል ለሠላም መከበር የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከረቱ አካላት ዕውቅና ተሰጠ

80

ሀዋሳ፣  መስከረም 21/2013 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል ለሠላምና ፀጥታ መከበር የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና ተሰጠ።

"ለሠላም እናመሰግናለን" በሚል መርህ ዛሬ በሀዋሳ በተካሄደው መድረክ በክልሉ መንግስት እውቅና ከተሰጣቸው መካከል አባ ገዳዎች፣የጎሳ መሪዎች፣ የሃገር ሽግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶችና ሲቪክ ማህበራት ይገኙበታል።

እንዲሁም በተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኙ  ለ2 ሺህ 401 የጸጥታ አስከባሪዎች በክልሉ ሠላምና ጸጥታ ቢሮ፣ በማረሚያና ፖሊስ ኮሚሽን አማካይነት የገንዘብ፣የዕርከንና የማዕረግ ዕድገት ተሰጥቷቸዋል።

እነዚህ አካላት ከ2010 ዓ.ም አጋማሽ ወዲህ በክልሉ ሲከሰቱ የነበሩ አለመረጋጋቶች ሰክነው ወደ ቀደሞ ሠላምና ልማት እንዲመለስ የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ተገልጿል።

በመድረኩ የተገኙት የደቡብ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በሃገሪቱ ለረጂም ዘመናት ሲሻገሩ የመጡ ጥያቄዎች መነሻ በማድረግ ለውጡን ለመቀልበስ  ሙከራዎች መደረጋቸውን ተናግረዋል።

የለውጥ ጉዞው በርካታ ፈተናዎች ቢያጋጥሙትም የቆዩ ሳንካዎችን በመፍታትና ጥያቄዎች በመመለስ  ሁለንተናዊ ብልጽግና ጉዞ ጀምረናል ብለዋል።

በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ የገጠመውን አለመረጋጋት ወደ ሰላማዊ ለማምጣት መንግስትና  ጸጥታ ኃይሉ  ከህዝቡ ጋር ተቀናጅተው በመሥራታቸው መሻገር መቻሉን ጠቅሰዋል።

ክልሉ ወደ ቀደመው ሠላምና ልማት እንዲመለስ  የላቀ አስተዋጽኦ ላማረከቱ አካላት መንግስት ዕውቅና  መስጠቱን ተናግረዋል።

በሃገሪቱ ባልተለመደ መልኩ በክፉዎች ጠንሳሽነት የተፈጠሩትን ግጭቶችና ጥፋቶች ለማስቆም፣አጥፊዎችን በመቅጣትና የተጎዱትን በማጽናናት ወንድማማችነትን ለማጠናከር ለተሳተፉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይም ዘላቂ ሠላምና ልማትን ለማጠናከር ከአጎራባች ክልሎች ጋር በጋራ እንደሚሠራ አቶ ርስቱ አስታውቀዋል፡፡

የክልሉ ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ በበኩላቸው ባለፉት ጊዜያት በክልሉ የገጠመው የጸጥታ ችግር በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን አውስተዋል።

በችግሩ የከፋ ጉዳት  እንዲደረስ የታለመ ቢሆንም በአጭሩ መቅጨት መቻሉን ገልጸዋል።

የህዝቦችን እንግልት ለማስቆም የተጣለባቸውን ኃላፊነት ለተወጡ የጸጥታ አስከባሪዎችና ሌሎችም አካላት መንግስት ዕውቅና መስጠቱ  በቀጣይ የተሻለ ለመስራት የሚያነሳሳ መሆኑን ተናግረዋል።

ባህላዊ መሠረቶችን በማጠናከርና ዘላቂ ሠላምን በመገንባት የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ማጠናከር እንደሚቻል ገልጸዋል።

የማዕረግ እድገትና  የገንዘብ  ሽልማት ከተበረከተላቸው መካከል የልዩ ኃይል አባል ብዙነሽ አበሻ በሰጠችው አስተያየት በደቡብ ኦሞ ዞን በተለያዩ ግዳጆች በመሰማራት ሠላምን ለማስከበር የድርሻዋን ስትወጣ መቆየቷን  ገልጻ ሽልማቱ   ለቀጣይ ስራዋ ብርታት እንደሚሆናት ተናግራለች።

በክልሉ በሚዛን ቴፒ አካባቢ ተፈጥሮ የነበረው የሰላም መደፍረስ ለማስተካከል  በግዳጅ ላይ እያለ የአካል ጉዳት እንደገጠመው የተናገረው ደግሞ ሌላው እውቅና የተሰጠው ረዳት ሳጂን አጥናፉ አድላየሾ  ነው።

ለሃገርና ህዝብ በማገልገሌ ደስታዬ ወደር የለውም ብሏል።

በመድረኩ ለኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳና ለሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ  ሌዳሞ  ሠላምን ለማረጋገጥ ላበረከቱት አስተዋፅኦ ባህላዊ  አልባሳትና ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም