ማዕከሉ ከ5 ተቋማት ጋር ለመስራት ስምምነቶችን ተፈራረመ

76

አዲስ አበባ፣መስከረም 21/2013 (ኢዜአ) አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ማዕከል ከአምስት ተቋማት ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነቶች ዛሬ ተፈራረመ፡፡

ከማዕከሉ ጋር  ለመስራት ስምምነቱን የፈረሙትዘውዲቱ ሆስፒታል፣አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ ብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ፣አዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩትና የኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ ናቸው፡፡

ስምምነቶቹ በፋይናንስ ፣በትምህርትና በጤና ዘርፎች በጋራ ለመስራት እንደሚያስችሉ ተገልጿል፡፡

አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ማሽኖች ሰው ሰራሽ የሆነ የማሰብ ክህሎትን በመጠቀም የሰው ልጅን በማገዝ በተለያዩ መስኮች እንዲሰማሩ የሚደረግበት ሳይንሳዊ አሰራር ነው።

በጤና፣ በግብርና፣ በትራንስፖርት፣ በሕዝብ ጥበቃና ደህንነትና በሌሎችም ዘርፎች ጥቅም ላይ በማዋል ለአገር ብልጽግና የሚረዱ የምርምር ውጤቶች ለማፍለቅ እየተሰራበት መሆኑም ተመልክቷል።

በማዕከሉ በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ ተቋማት ጋር የምርምር ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተነግሯል።

በተለይ በጡት ካንሰር፣ በኢንተለጀንስ የትራንስፖርት ሥርዓት፣ በፋይናንስና በግብርና ዘርፎች የሚካሄዱት ምርምሮች ተስፋ ሰጪ መሆናቸው ተገልጿል።

ማዕከሉ ለውጥ የሚያመጡና ወደተግባር የሚለወጡ ቴክኖሎጂዎች በተቀናጀ መልኩ ለማፍለቅ መቋቋሙ በቅርቡ ምረቃው በተካሄደበት ሥነ ሥርዓት ላይ መገለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም