የኢሬቻ በዓል ታዳሚዎች ለኮቪድ 19 ወረርሺኝ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የጤና ሚኒስትሯ አሳሰቡ

84

አዲስ አበባ፣መስከረም 21/2013 (ኢዜአ) የኢሬቻ በዓል ታዳሚዎች ለኮቪድ- 19 ወረርሺኝ ተጋላጭ እንዳይሆኑ በጥንቃቄ ማክበር እንዳለባቸው የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አሳሰቡ።

ሚኒስትሯ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የኢሬቻ በዓል በመሰባሰብ የሚከበር ማኅበራዊ ግንኙነቶችንና ትስስሮች የሚጠናከሩበት ታላቅ በዓል ነው።

ይሁን እንጂ በዓለምና በአገር አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሺኝ ምክንያት ይህን በዓል በተለየ መልኩ ማክበር ይገባል ብለዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በወረርሺኙ የሚጠቁ፣ በጽኑ የሚታመሙና ለህልፈተ ህይወት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱንም አንስተዋል።

እስካሁን ምርመራ ከተደረገላቸው ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከ75 ሺህ በላይ የሚሆኑት በቫይረሱ መያዛቸውን ጠቅሰዋል።

በቫይረሱ ህይወታቸው ያለፈው ሰዎች ቁጥርም 1 ሺህ 198 መድረሱንና አሁን ላይ 269 ሰዎች በጽኑ መታመማቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም ኢሬቻ በሚከበርበት ወቅት እነዚህን ሁኔታዎች ከግምት በማስገባት የቫይረሱን ተጋላጭነት መቀነስና በጥንቃቄ ማክበር እንደሚገባ ዶክተር ሊያ አሳስበዋል።

የበዓሉ ታዳሚዎች ርቀትን መጠበቅ እንዲሁም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎችን ማድረግ ይኖርባቸዋልም ብለዋል።

በአከባበሩ ወቅት እንደ ወትሮው በርካታ ሰዎች መሰባሰብ አይኖርባቸውም ያሉት ሚኒስትሯ ሁሉም በያሉበት ሆነው መርሃ ግብሩን በሚካሄደው የቀጥታ ስርጭት ቢከታተሉ መልካም ነው ብለዋል።    

አሁን ላይ እንቅቃሴዎች የተከፈቱት ቫይረሱ ከዚህም በኋላ የሚቆይ መሆኑን ከግንዛቤ በመውሰድና ኅብረተሰቡም አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ በማሳብ መሆኑን ገልጸዋል።

በሽታው ስለሌለ ሳይሆን ከወረርሺኙ ጋር ህይወት ማቀጠል ስለሚያስፈልግና "ካሉት አስቸጋሪ ሁኔታዎች የተሻለውን አስቸጋሪ ሁኔታ በመምረጥ ነው" ብለዋል።

ያም ሆኖ አሁን ላይ ኅብረተሰቡ እየተዘናጋ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ አሁንም ወቅቱ የወረርሺኝ በመሆኑ ኅብረተሰቡ የሚያደርገውን ጥንቃቄ ሊያጠናክር እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሚኒስትሯ ለመላው የኢሬቻ በዓል ታዳሚዎችና ተሳታፊዎች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም