በአዲስ አበባ ለሚከበረው የኢሬቻ በዓል በቂ ዝግጅት መደረጉን የከተማ አስተዳደሩ ገለጸ

162

አዲስ አበባ፣መስከረም 21/2013 (ኢዜአ) የፊታችን ቅዳሜ በአዲስ አበባ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል በአብሮነትና በመከባበር መንፈስ እንደሚከበር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ዣንጥራር አባይ ተናገሩ።

የፊታችን ቅዳሜ በአዲስ አበባ ለሚከበረው የኢሬቻ በዓል የከተማ አስተዳደሩ በቂ ዝግጅት ማድረጉንም ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የተወከሉ ነዋሪዎች የኢሬቻን በዓል በፓናል ውይይት አክብረውታል።

በከተማ አስተዳደሩ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ዣንጥራር አባይ በውይይቱ ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት ኢሬቻ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው በዓል እንዲሆን ባህላዊ እስቱን ጠብቆ ይከበራል።

ክብረ በዓሉ የኦሮሞ ህዝብ የሚታወቅበትን የአቃፊነትና አብሮ የመኖር እሴቱን በሚያጠናክር መልኩ እሴቱን ጠብቆ በመዲናዋ ይከናወናል ብለዋል።

ኢሬቻ ''በሰላም አብሮ የመስራት፣ በጋራ የማደግና ፍቅር የምናስተላልፍበትና በጋራ አገር ለመገንባት የሚያስችል አንድ መገለጫ ነው'' ብለዋል።

በዓሉን በሰላም፣ በአብሮነትና አንድነታችንን በሚያጠናክር መልኩ ለማክበር ሁላችንም ዝግጁ መሆን አለብን ነው ያሉት አቶ ዣንጥራር።

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የክብረ በዓሉ ባለቤት በመሆን በጋራ በመቆምና እንግዶችን ተቀብሎ በማስተናገድ እንዲያከብሩትም ጠይቀዋል።

የፊታችን ቅዳማ በአዲስ አበባ ለሚከበረው የኢሬቻ በዓል የከተማ አስተዳደሩ በቂ ዝግጅት ማድረጉንም ገልጸዋል።

''ኢሬቻ የኢትዮጵያዊያን ሁሉ የጋራ እሴት በመሆኑ ታሪኩንና ትውፉቱን ጠብቆ እንዲያድግ ለክብረ በዓሉ በጋራ መስራት አለብን" ያሉት ደግሞ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ በላይ ደጀን ናቸው።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አንዳንዶቹ እንዳሉት ኢሬቻ ሰላምን፣ ፍቅርን አብሮነትንና መልካም ተስፋን የሚያመላክት የጋራ ሃብት በመሆኑ በጋራ ልናሳድገውና ልንጠብቀው ይገባል ብለዋል።

ኢሬቻና መሰል ህዝባዊ በዓላት ዘመናትን ያስቀጠሉ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ የመጡ የጋራ መገለጫዎች መሆናቸውን አንስተዋል።

አቶ ሓብታሙ ጉደታና አቶ ተስፋየ ገመዳ የተባሉት አስተያየት ሰጭዎችም አገራዊ በዓላትን በጋራ ማክበሩ አንድነትን ያጎለብታል ብለዋል።

የብሔር ብሔረሰቦች መገለጫ የሆኑ በዓላት በሚከበሩበት ጊዜ ሁሉም የሚሳተፉበት መድረኮች ቢኖሩ የተሻለ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኢሬቻ በዓል በዓመት ሁለት ጊዜ የሚከበር ሲሆን አንዱ ክረምት ሳይገባ አባ ገዳዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና እናቶች ወደ ተራራማ ስፍራ በመሄድ ፈጣሪን የሚለምኑበት ''ኢሬቻ ቱሉ'' በመባል ይታወቃል።

ሁለተኛው  ደግሞ ክረምት አልፎ ጸደይ ሲመጣ አዝመራ ሲደርስ ለምስጋና ወደ ውሃ ስፍራ በመሄድ የሚደረገው ''ኢሬቻ መልካ '' ወይም የምስጋና በዓል በመባል የሚታወቅ ነው።

የኢሬቻ 'ሆራ ፊንፊኔ' በመጪው ቅዳሜ በአዲስ አበባ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም