በትግራይ ምዕራባዊ ዞን የቤት እንስሳት ጤንነት ለመጠበቅ የክትባት ዘመቻ እየተካሄደ ነው

57

ሁመራ፣ መስከረም 21/2013 (ኢዜአ ) በትግራይ ምዕራባዊ ዞን ከአንድ ሚሊዮን ለሚበልጡ የቤት እንስሳት ጤንነት ለመጠበቅ የበሽታ መከላከያ ክትባት በዘመቻ እየተሰጠ የዞኑ የእንስሳት ጤና ጽህፈት ቤት ገለጸ።

ካለፈው ነሐሴ ወር መጨረሻ  ጀምሮ በዘመቻ እየተሰጠ ያለው ክትባት ለቀንድ ከብቶች ፣በጎችና ፍየሎች የቆዳ በሽታ መከላከያ  መሆኑን  በጽህፈት ቤቱ  የእንስሳት ጤና ባለሙያ አቶ ሐጎስ ጸጋይ ለኢዜአ ተናግረዋል።

እስካሁንም ከ260 ሺህ ለሚበልጡ  እንስሳት ክትባት መሰጠቱን ጠቁመው ቀሪዎችንም ለማዳረስ ስራው መቀጠሉን አስረድተዋል።

በዞኑ በየዓመቱ በተመሳሳይ ወቅት በቫይረስ ምክንያት ከእንስሳት ወደ እንስሳት የሚተላለፈው "አፍተግር"   በሽታን ለመከላከልም   ክትባት ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

"የአፍተግር " ከቀንድ ከብቶች ባለፈ በጎችና ፍየሎችን በማጥቃት የሚታወቅ በሽታ መሆኑን ባለሙያው ገልጸዋል።

በአካባቢው ከሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች ጋር በመተባበር በሽታው ከመከሰቱ በፊት አስቀድመው ለመከላከል በቂ ስልጠናና ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

በዞኑ ቃፍታ ሁመራ ወረዳ የማይቀይሕ ቀበሌ አርሶ አደር ኪዳነ ገብረዋሂድ በሰጡት አስተያየት  ከአንድ ሳምንት በፊት 25 የቀንድ ከብቶቻቸውን ከበሽታ ለመጠበቅ ማስቻሉን ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት በከብቶቻቸው ላይ የጤና ችግር ይደርስባቸው እንደነበር የተናገሩት  ደግሞ በወረዳው የራዊያን ቀበሌ አርሶ አደር መብራህቱ ወለንሰአ ናቸው።

አሁንም ከብቶቼን በበሽታ ሊጠቁ ይችላል የሚል ስጋት ነበረብኝ ብለዋል።

ሆኖም ዘንድሮ ወቅቱን ጠብቆ በተደረገው የክትባት ዘመቻ ያሏቸውን የቀንድ ፣  ፍየሎችና የጋማ ከብቶቻቸውን የቆዳ በሽታ መከላከያ ክትባት እንደተደረገላቸው ገልጸዋል።

በምዕራባዊ ዞን በቅርብ ጊዜ በተደረገው ቆጠራ ከአንድ ሚሊዮን 500 ሺህ  በላይ የተለያዩ የቤት እንስሳት እንደሚገኙ መታወቁን ከእንስሳት ጤና ጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም