የኢትዮጵያ ከፍተኛ የልኡካን ቡድን ከሱዳን ሉኣላዊ ምክር ቤት ሊቀ መንበር ጋር ተወያየ

55

አዲስ አበባ፣ መስከረም 21/2013 ( ኢዜአ)  በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው የተመራው የኢትዮጵያ ከፍተኛ የልኡካን ቡድን ከሱዳን ሉኣላዊ ምክር ቤት ሊቀ መንበር እና ሌሎች የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር መወያየቱ ተገልጿል፡፡

የልኡካን ቡድኑ ትላንት በካርቱም ባደረገው ቆይታ ከሱዳን ሉኣላዊ ምክር ቤት ሊቀ መንበር፣ ከሉአላዊ ምክር ቤቱ ምክትል ሊቀመንበር፣ ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር እና  ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር ተወያይቷል።

ውይይታቸውም በሁለቱ አገሮች ግንኙነት መጠናከር ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።

ከልኡካን በድኑ አባላት የኢፌዴሪ መከላከያ ኤታማጆር ሹም ጄነራል አደም መሃመድን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ይገኙበታል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገዱ አንዳርጋቸው ከሱዳኑ አቻቸው ጋር በነበራቸው ውይይት በኢትዮጵያም በተለያዩ አካባቢዎች ተመሳሳይ የጎርፍ አደጋ ያጋጠመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሱዳን ሕዝብ ላይ የደረሰውን የተፈጥሮ አደጋ ለመታደግ  የአቅሟን ማድረጓ የሁለቱን አገሮች የቆየ ዝምድና ለማጠናከርና በችግር ወቅትም አብረን መሆናችንን ለማረጋገጥ  ነው ብለዋል።

የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦማር ቀመር-አልዲን እስማኤል በበኩላቸው በኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ለተደረገው የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የሁለቱ አገር ህዝቦች የሚያጋጥሟቸውን መሰል ተግዳሮቶች በትብብር ለመቅረፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተቀራርበው ይሰራሉ ብለዋል።

የልኡካን ቡድኑ በሱዳን በጎርፍ አደጋ ለተጎዱ የአልሚ ምግብ፣ መድሃኒት እና ሌሎች የሰብአዊ እርዳታዎችን አድርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም