በሶስት ከተሞች በ53 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተገነቡ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ተመረቁ

82

አዲስ አበባ፣ መስከረም 21/2013 ( ኢዜአ) በቢሸፍቱ፣ዱከምና በሞጆ ከተሞች በ53 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተገነቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ዛሬ ተመረቁ፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎቹን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ መርቀው ከፍተውታል።

ጣቢያዎቹ ለከተሞቹናአካባቢያቸው እንዲሁም በዙሪያቸው ለሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የኃይል ፍላጎት ምላሽ ለማሟላት የተገነቡ ናቸው፡፡

ከፍተኛ የኃይል ጫናና መቆራረጥ ችግሮችም ይቀንሳል፡፡

ከአዲስ አበባ በ30 ኪሎ ሜትር ርቀት በዱከም ከተማ የተገነባው ባለ 230/15 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የግንባታ፣ ፍተሻና የሙከራ ሥራው ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቁ ተገልጿል፡፡

ከአዲሱ የቢሾፍቱ 400 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ተነስቶ እስከ ዱከም ማከፋፈያ ድረስ 16 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ጥንድ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መሥመር ዝርጋታም ተከናውኗል፡፡

በሞጆ ከተማ የተገነባው ባለ 230 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያም በተመሳሳይ ግንባታ፣ ፍተሻና ሙከራው ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል፡፡

የዱከምና የሞጆ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ጥንድ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ገቢ መሥመርና 10 ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጪ መሥመሮች ያሏቸው ሲሆን፣ ሁለት ባለ 50 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመሮች ተተክለውላቸዋል፡፡

የጣቢያዎቹ ግንባታ በሕንድ፣በቦስኒያ ሄርዞጎቢኒያና በኢትዮጵያ ሥራ ተቋራጮች መካፈላቸው ታውቋል፡፡

በአማካሪነት ደግሞ የጀርመንና ስዊዘርላንድ ኩባንያዎች ተሳትፈዋል፡፡

ግንባታው 85 በመቶ ከፈረንሳይ ልማት ባንክ በተገኘ ብድርና በኢትዮጵያ መንግሥት 15 በመቶ ወጪ መከናወኑ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም