በኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት ውሳኔ መሰረት የኢሬቻ በዓልን ማክበር እንደሚገባ አባገዳና ሀዳ ሲንቄ ተናገሩ

122

አዳማ፣ መስከረም 21/2013 (ኢዜአ) ኢሬቻ ፖለቲካ የሌለው የምስጋና ቀን በመሆኑ ኮሮናን ለመከላከል በኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት በተላለፈው ውሳኔ መሰረት በዓሉን ማክበር እንደሚገባ አባገዳ፣ ሀዳ ሲንቄ እና ወጣቶች ተናገሩ።

የአዳማና አካባቢዋ የቱለማ አባገዳ መግራ ለገሰ ለኢዜአ እንዳሉት ኢሬቻ ፖለቲካ የለውም፤ የምስጋና የእርቅ ቀን በመሆኑ ወጣቶች ለአፍራሽ ኃይሎች አሉባልታ ቦታ ሳይሰጡ የአባገዳዎችን ውሳኔ ተቀብለው ተግባራዊ ማድረግ ይገባቸዋል።

በኦሮሞ አባገዳዎች የተላለፈውን ውሳኔ ሰላም የማይፈልጉ ኃይሎች ኢሬቻ ለፖለቲካ ፍጆታ ነው የዋለው እያሉ ህብረተሰቡን በተለይ ወጣቱን  በተራ አሉባልታ እያሳሳቱ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢሬቻ  የሰላም፣ የፍቅርና የምስጋና ቀን በመሆኑ የኮሮና በሽታ ከሀገሪቱ  ከጠፋ ወጣቱ ሌላውም የህብረተሰብ ክፍል አንድ ላይ ሆነን አብረን ማክበር እንችላለን  ያሉት አባገዳው፤ ሆኖም  አሁን በበሽታው ምክንያት በዓሉ በውስን ሰው ስለሚከበር ሁሉም ይህንን ማክበር እንዳለበት አመልክተዋል።

በአዳማና አካባቢዋ ያሉ ወጣቶችና ሴቶች በያሉበት ቦታ ሆነው እንዲያከብሩ እየመከርን ነው፤ ወጣቶችም ምክራችንን ሰምተው ለመተግበር ዝግጁ ናቸው ብለዋል።

የአባ ገዳዎች መልዕክት መከበር አለበት፤ ወጣቱ የአባገዳዎችን ጥሪ ወደ ጎን በመተው መሄድ የለበትም፤ ከዚህ ውጭ ያለው አካሄድ ከኦሮሞ ባህልና ወግ ያፈነገጠ ተግባር ነው የሚሆነው ትንሹም ትልቁም መደማመጥ አለብን ያሉት ደግሞ የቱለማ ኦሮሞ ሀዳ ሲንቄ ወይዘሮ ጫሊ ቱምሳ ናቸው።

ከውሳኔው ውጭ በዓሉን ለማክበር መሄድ ለበሽታው መጋለጥ መሆኑን ገልጸው፤ በእልህ በመንቀሳቀስ የበዓሉን ሰላምና ስኬት ለማስጠበቅ ከተሰማራው የፀጥታ ኃይል ጋር መጋጨት ተገቢነት እንደሌለው ተናግረዋል።

ኢሬቻን ዘንድሮ እንደ አምናው ህዝቡ በብዛት ወጥቶ ማክበር  ያልተቻለው  በኮሮና ምክንያት መሆኑን ጠቅሰው፤ የሰዎችን ህይወት ከበሽታው ለመታደግ  የተላለፈውን ውሳኔ ማክበርና ተገዥ መሆን አለብን ብለዋል።

አንድ ሰው በበዓሉ ላይ በሽታውን ይዞ ወደ ቤቱ ከገባ  ተጨማሪ ጉዳት በመሆኑ ይሄ ክፉ ጊዜ ካለፈ እንደወትሮው ሁሉ ሁሉም በአንድነት ማክበር ስለሚቻል ሁላችን ውሳኔውን ማክበር ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ከአዳማ ከተማ ወጣቶች መካከል  ሰኚ ቱምሳ በሰጠው አስተያየት ኢሬቻ ሰላም በመሆኑ ወጣቱ ለበዓሉ ስኬት የተባለውን መስማት አለበት ብለዋል።

በሽታው እንዳይስፋፋና የዜጎች ደህንነት እንዲጠበቅ አባገዳዎች ያሳለፉት ውሳኔ ተገቢ መሆኑን የገለጸው ወጣት ሰኚ፤ ህዝቡ በብዛት  ሆኖ የዘንድሮውን ኢሬቻ እንዳያከብር እንጂ የተላለፈው ውሳኔ  ለፖለቲካ ጉዳይ አይደለም  ሲል ተናግሯል።

ውሳኔውን ወደ ጎን በመተው ሰው መሄድ እንደሌለበት ጠቁሞ፤  የመግቢያ  ባጁን የወሰዱና አባገዳዎች በዓሉን አክብረው በሰላም እንዲመለሱ የሚደግፍ መሆኑን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም