በተለምዶ ጣሊያን ሰፈር ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ፈርሰው የታደሱ አምስት የአቅመ ደካሞች ቤቶች ርክክብ ተካሄደ

76

አዲስ አበባ  መስከረም 20/2013 (ኢዜአ) በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ ሁለት በተለምዶ ጣሊያን ሰፈር ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ፈርሰው የታደሱ አምስት የአቅመ ደካሞችን ቤቶች ርክክብ ተካሄደ። 

የቤቶቹ ዕድሳት የተካሄደው ወረዳው ከጣሊያን ሰፈር ልጆች በጎ አድራጎት ማህበር ጋር በመተባበር ነው።

የማህበሩ ሰብሳቢ ወጣት ዘላለም ብርሃኑ  የፈረሱ ቤቶችን በማድስ አቅመ ደካሞችና አረጋዊያን  የተሻለ ቤት አግኝተው ማየት የሁሉም ፍላጎት መሆኑን ገልጿል።

ይህንን ፍላጎት እውን ለማድረግ በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጾ፤ የማህበሩ አባላት ላሳዩት የትብብር ስራ ምስጋና አቅርቧል።

ማህበሩ በማህበራዊ አገልግሎቶች ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝ በመግለጽ፤ ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ቤቶችን የማደስና የኩላሊት ህሙማንን ማሳከምን ጨምሮ የተለያየ ስራዎች ማከናወኑን አስታውሰዋል።

በቀጣይም የማህበሩ የመልካም አድራጎት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጿል።

የአራዳ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አበባ እሸቴ የጣሊያን ሰፈር ልጆች በጎ አድራጎት ማህበር ላደረገው መልካም ተግባር ያላቸውን አድናቆት ገልጸው ምስጋና አቅርበዋል።

ማህበሩ ማዕድ በማጋራት ረገድ ሰፊ ስራ ሲሰራ መቆየቱን በማስታወስ ይህ በጎ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

የወረዳው ምክትል ዋና ስራ አሰፈፃሚ ወይዘሮ ምንታምር አሌማ በበኩላቸው በአካባቢው በርካታ አቅመ ደካሞች ቤት ችግር ያለበት በመሆኑ በትብብር ማደስ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የዛሬውን ጨምሮ በወረዳው 19 የአቅመ ደካሞች ቤቶች መታደሳቸውን ጠቅሰዋል።

ቤት ከታደሰላቸው መካከል አንዷ የሆኑት ወይዘሮ መዲና ቢላል ሰባት ልጅ ይዘው ዝናብና ፀሃይ እየተፈራረቀባቸው በከፍተኛ ችግር እንደነበሩ አስታውሰው ለተደረገላቸው ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

የቤት እድሳቱ ተጠቃሚ የሆኑት በሙሉ መደሰታቸውን ገልጸው የጣሊያን ሰፈር ልጆች በጎ አድራጎት ማህበርን አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም