የኢሬቻን ባዓል በፍቅርና አብሮነት እንግዶችን በመቀበል ለማክበር ተዘጋጅተናል- ነዋሪዎች

63

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20/2013 (ኢዜአ) በመጪው ቅዳሜ ''በሆራ ፊንፊኔ'' ለሚከበረው የኢሬቻ በዓል በአብሮነትና በሰላም እንግዶችን በመቀበል ለማክበር መዘጋጀታቸውን በአዲስ አበባና አካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች ገለጹ።

በአዲስ አበባ የኢሬቻ በዓል ዝግጅትን በተመለከተ ከየካና ቦሌ ክፍለ ከተሞች እንዲሁም ከመዲናዋ አቅራቢያ ጣፎ፣ ሱሉልታ እና ሰንዳፋ ከተሞች የተውጣጡ ነዋሪዎች ውይይት አድርገዋል።

የየካ ክፍለ ከተማ ዋና ስራአስፈጻሚ አቶ አስፋው ለገሰ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የገዳ-ስርዓት አንዱ አካል የሆነውን የኢሬቻ በዓል በሰላምና አብሮነት ልናከብረው ይገባል ብለዋል።

የኢሬቻ በዓል የአንድነት፣ የፍቅር፣ አብሮነትና ሰላም መገለጫ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የፊታችን ቅዳሜ በአዲስ አበባ የሚከበረውን በዓል እንግዶችን በማክበርና በማስተናገድ አብሮነትና ፍቅር ለማክበር ዝግጁ መሆን አለብን ብለዋል።

የኦሮሞ የባህል ሊሂቃን የሆኑት ሃዩ ዘውዱ መርጋ በበኩላቸው በተለይ ወጣቶች ለሰላም ዘብ በመቆም ለበዓሉ ሰላመዊ አከባበር ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ መሰሉ ሂርጳ በዓሉን ከኮቪድ ራሳችንን እየጠበቅን በሰላምና አብሮነት መንፈስ ለማክበር ተዘጋጅተናል ብለዋል።

የኢሬቻ በዓል በዓመት ሁለት ጊዜ የሚከበር ሲሆን አንዱ ክረምት ሳይገባ አባ ገዳዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና እናቶች ወደ ተራራማ ስፍራ በመሄድ ፈጣሪን የሚለምኑበት ''ኢሬቻ ቱሉ'' በመባል ይታወቃል።

ሁለተኛው  ደግሞ ክረምት አልፎ ጸደይ ሲመጣ አዝመራ ሲደርስ ለመስጋና ወደ ውሃ ስፍራ በመሄድ የሚደረገው ''ኢሬቻ መልካ '' ወይም የምስጋና በዓል በመባል የሚታወቅ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም