ፓርኩ የውጭ ሀገራት መሪዎች ሀዋሳን እንዲገበኙ መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል---በሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች

61
ሀዋሳ ሐምሌ 7/2010 የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የውጭ ሀገራት መሪዎች ከተማውን እንድጎበኙ መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን ሀዋሳ ከተማ ኢዜአ ያነጋገራቸው  ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ ፓርኩ ከተቋቋመበት ዋነኛ ዓላማ ጎን ለጎን የገፅታ ግንባታ ሚና በመጫወት ላይ እንደሚገኝ የፓርኩ ስራ አስኪያጅ ገልጸዋል፡፡፡ ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ አስራት አላሮ "የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለከተማውና አካባቢው ወጣቶች የስራ እድል ከመፍጠርና ሰፊ የኢኮኖሚ ጥቅም ከማበርከቱም  በተጨማሪ በበርካታ እንግዶች ከተማዋን እንዲጎበኟት እድል ፈጥሯል "ብለዋል፡፡ በየጊዜው እየመጡ ከሚጎብኙ እንግዶች በተጨማሪ በፓርኩ በርካታ የውጭ ዜጎች መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ በመሆናቸው የከተማውን የንግድ እንቅስቃሴ አጠናክሯል፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርክ ለከተማው ሁለንተናዊ እድገት ብቻ ሳይሆን የሚያበረክተው ማህበራዊ ፋይዳም   የጎላ መሆኑን ያመለከቱት አቶ መሐመድ ሁሴን የከተማዋ ነዋሪ ናቸው፡፡ "ፓርኩን ለመጎብኘት የሚመጡ የየሀገሪቱ መሪዎች ከተማችንንም ስለሚጎበኙ የከተማውን ገፅታ የመገንባት አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው "ብለዋል፡፡ በአሜርካን ሃገር ኑሮዋን ከመሰረተች አራት ዓመታትን ያስቆጠረችውና የሃዋሳ ተወልጇ ወይዘሮ ሮማን አበራ ስለ ፓርኩ በቂ እውቀት ባይኖራትም በተደጋጋሚ የሃገር መሪዎች እንደሚጎበኙት የምታውቅ መሆኗን ተናግረዋል፡፡ "ለአለም ምሳሌ ሊሆን የሚችል ስራ እንደሚሰራባት አምናለሁ" ያሉት አስተያየት ሰጪዋ ሃዋሳ በተለያዩ ሃገር መሪዎች እንድትጎበኝ እድል የፈጠረና በዚህም  ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ዛሬም በዚህ ታሪካዊ ቀን ሃዋሳ ላይ መገኘታቸው እንዳስደሰታቸውና  መሪዎቹን ለመቀበል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡ የሀዋሳ ኢንዳስትሪ ፓርክ ስራ አስኪያጅ አቶ በላይ ኃይለሚካኤል እንዳሉት ፓርኩ ተገንብቶ ስራ ከጀመረበት ማግስት አንስቶ የተለያዩ ሀገራት  መሪዎች ኢትዮጵያ ሲገቡ የሀዋሳን ኢንዱስትሪ ፓርክ ይጎበኛሉ፡፡ እስከ አሁን የቀድሞ የላይበሪያ ፕሬዝዳንት የነበሩት ኤሌን ጆንሰን፣ የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር ፣ የሩዋንዳው ፖልካጋሜ የሀዋሳን ኢንዱስትሪ ፓርክ ከገበኙት መካከል ይገኙበታል፡፡ በተመሳሳይ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት በተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ዋና ስራ አስፈፃሚ እንዲሁም የተለያዩ ሃገራት አምባሳደሮች ፓርኩን ጎብኝተዋል፡፡ በተጨማሪም የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ዛሬ ፓርኩን መጎብኘታቸው   ያመለከቱት አቶ በላይ "የእሳቸው ጎብኝት ታሪካዊ ነው "ብለዋል፡፡ ፓርኩ ከተቋቋመበት ዋነኛ ዓላማ ጎን ለጎን የገፅታ ግንባታ ሚና በመጫወት ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ "ሀገራት በዘርፉ ልምድ እንዲለዋወጡ ስለሚያደርግ በጋራ ለመስራት በሚችሉባቸው የአገር ለአገር ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት በር ይከፈታል" ብለዋል አቶ በላይ፡፡ የሚሰጧቸው ግብረ መልሶች  መንግሥት እንደሀገር ለዘርፉ እድገት ተነሳሽነት እንደሚያሳደግ የገለጹት ስራ አስኪያጁ ጉብኝት ያደረጉ ሀገራት መጥተው መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ  እድል እንደሚፈጥርም አመልክተዋል፡፡ የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በወር እስከ 24 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ እያስገኘ መሆኑንና  ለ18 ሺህ ዜጎች የስራ እድል መፍጠሩን ስራ አስኪያጁ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም