አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ለ40 ተጫዋቾች ጥሪ አደረጉ

114

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20/2013 (ኢዜአ) አዲስ የተሾሙት የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ለአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ለ40 ተጫዋቾች ጥሪ አደድርገዋል።

ከሽመልስ በቀለ ውጪ የተቀሩት ተጫዋቾች በአገር ውስጥ የሚጫወቱ ናቸው።

አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከትናንት በስቲያ የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ሆነው በይፋ መሾማቸው የሚታወስ ነው።

በካሜሮን ለሚካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ የሚደረጉ የማጣሪያ ጨዋታዎች በኅዳር ወር 2013 ዓ.ም ዳግም ይጀመራሉ።

በምድብ 11 ከማዳጋስካር፣ ኮትዲቭዋርና ኒጀር ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ከኒጀር አቻው ጋር በሜዳውና ከሜዳው ውጪ ጨዋታውን ያደርጋል።

አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከኒጀር አቻው ጋር ላለበት ጨዋታ ለ40 ተጫዋቾች ጥሪ ማድረጉን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

ለግብጹ ምስር ኤል ማክሳ ክለብ ከሚጫወተው ሽመልስ በቀለ ውጪ ሌሎቹ ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች በአገር ውስጥ ሊግ የሚጫወቱ ናቸው።

ጥሪ ከተደረገላቸው መካከል የቅዱስ ጊዮርጊሱ ጌታነህ ከበደ፣ የመቐለ ሰባ እንደርታው አማኑኤል ገብረሚካኤል፣ የሰበታ ከተማው ዳዊት እስጢፋኖስ፣ የፋሲል ከነማው ሱራፌል ዳኛቸው፣ የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ነስሩ፣ የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይና የመከላከያው ግብ ጠባቂ አቤል ማሞ ይገኙበታል።

ተጫዋቾቹ እስከ መስከረም 23 ቀን 2013 ዓ.ም በፌደሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ተገኝተው ሪፖርት እንደሚያደርጉና የኮሮናቫይረስ ምርመራ እንደሚደረግላቸው ተገልጿል።

ቡድኑ ዝግጅቱን አዲስ አበባ በሚገኘው የካፍ አካዳሚ እንደሚያደርግና ፌዴሬሽኑ አካዳሚውን ለልምምድ ዝግጁ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል።

በተጨማሪም አሠልጣኝ ውበቱ አባተ አብረዋቸው የሚሠሩ ረዳት አሠልጣኞችን ዝርዝር ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሳውቀዋል።

በዚሁ መሠረት ደሳለኝ ገብረጊዮርጊስ የግብ ጠባቂ አሠልጣኝ እንዲሁም አንዋር ያሲንና አሥራት አባተ ምክትል አሰልጣኞች ሆነዋል።

በሂደት ሌሎች የአሠልጣኝ አባላትም ብሔራዊ ቡድኑን እንደሚቀላቀሉ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ አመልክቷል።

ውበቱ አባተ የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ለማሠልጠን የሁለት ዓመት ውል የፈረሙ ሲሆን በውሉ መሠረት ብሔራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ የማሳለፍ ግዴታ ተጥሎባቸዋል።

ዋልያዎቹ በማጣሪያው በሚገኙበት ምድብ 11 የኮትዲቯር አቻውን አሸንፎ በማዳጋስካር ተሸንፎ በሦስት ነጥብ ከማዳጋስካር በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን በመጋቢት ወር 2013 ዓ.ም ከኮትዲቯርና ማዳጋስካር ጋር ቀሪ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎቹን ያደርጋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም