የትራንስፖርት ዘርፉን ለአካባቢ ተስማሚ ለማድረግ የግሉ ዘርፍ መጠናከር አለበት

86

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የትራንስፖርት አገልግሎትን ከብክለት የጸዳና ለአካባቢ ተስማሚ ለማድረግ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ መጎልበት አለበት ተባለ።

የትራንስፖርት ሚኒስቴር የታዳሽ ኃይል ትራንስፖርትን በኢትዮጵያ ማስፋፋት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ውይይት አድርጓል።

በውይይቱ የተሽከርካሪ አስመጪ፣ ገጣጣሚና አምራች ድርጅቶች ኃላፊዎችና ተወካዮች ተገኝተዋል።

የታዳሽ ኃይል ትራንስፖርትን በኢትዮጵያ በማስተዋወቅ ተሞክሮ ያካፈሉት የማራቶን ሞተር መሥራችና ዋና ሥራአስፈጻሚ አቶ መልካሙ አሰፋ በዘርፉ ያለውን ምቹ ሁኔታና ተግዳሮት አስረድተዋል።

የግል ዘርፉ በታዳሽ ኃይል ዘርፍ ቢሰማራ ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለው የማይበገር አረንጓዴ ምጣኔ ሀብት ይበልጥ አዋጭ እንደሚሆን ከተሞክሯቸው አጋርተዋል።

መንግሥት በኤክሳይዝ ታክስ ላይ ያደረገው ማሻሻያ በታዳሽ ኃይል ትራንስፖርት ለመግባት እንዳበረታታቸው ገልጸዋል።

ዘርፉ በኢትዮያ አዲስ በመሆኑ ከፖሊሲ፣ መመሪያ፣ የሰው ኃይል ልማትና የገንዘብ አቅርቦት ሁኔታ መፈተሽ እንዳለበት ያነሱት የውይይቱ ተሳታፊዎች፤ መሠረተ ልማቶችም መታየት አለባቸው ብለዋል።

በዘርፉ ያላቸውን ተሳትፎ ለማጎልበትም እገዛ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

የትራንስፖርት ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ ''የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ አገር ውስጥ ማስገባትና ማምረት በመንግሥት አቅም ብቻ የሚተገበር አይደለም'' ብለዋል።

የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪውን በማዘመን በታዳሽ ኃይል የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባትና ለማምረት የግሉ ዘርፍ ወሳኝነትን በአጽእኖት አንስተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ያነሷቸውን ሥጋቶች ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመሆን ለማመቻቸት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።

በዘርፉ ለሚሰማሩ የተለያዩ የማበረታቻዎች ሥርዓቶችን በመዘርጋትና በመደገፍ እንዲሁም ችግሮችን በመፍታት ለዘርፉ ዕድገት ትኩረት እንደሚሰጥም ጨምረዋል።

ዘርፉን ከማዘመን፣ ተወዳዳሪ ከማድረግ፣ የሥራ ዕድል ከመፍጠር፣ ምቹ የትራንስፖርት አገልግሎት ከማቅረብ፣ ሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀትን ከመቀነስ አንጻር በኢትዮጵያ ያሉ ምቹ ሁኔታዎችና ተግዳሮቶች ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በዓለም ላይ 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን የኤሌክትሪክ መኪናዎች እንደሚገኙ መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም