የህዝቡን የአብሮነት እሴቶች ማጠናከር እንደሚገባ ተመለከተ

87

ጋምቤላ፣ መስከረም 20/2013 (ኢዜአ) በሀገሪቱ የሚታዩ የተዛቡ አመለካከቶችን በማስወገድ የህዝቡን የአንድነትና የአብሮነት እሴቶች ማጠናከር እንደሚገባ ተመለከተ።

የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከንግድ ባንክ ጋር በመተባበር በሰላም፣ አብሮነት፣ ኃይማኖትና ብዝሃነት ዙሪያ በጋምቤላ ከተማ ያዘጋጀው የውይይት መድረክ  ከባለድርሻ አካላት ጋር እያካሄደ ነው።

የጉባኤው ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቅ ትጉሐን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በውይይት መድረኩ እንዳሉት ባለፉት ጊዜያት የተሰሩ መልካም ያልሆኑ ተግባራት በሀገሪቱ የነበሩ የአንድነትና አብሮነት እሴቶችን ሸርሽረዋል።

በአሁኑ ወቅት እየታዩ ያሉት የግለኝነትና የጥላቻ አስተሳሰቦች በህዝቦች መካከል የነበረውን የመከባበርና በሰላም አብሮ የመኖር እሴቶችን እያቀጨጨና  ግጭት እየተከሰተ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት የተፈጠሩ መርዛማ አስተሳቦችንና አመለካከቶችን በማረም የህዝቡን የአንድነትና የአብሮነት እሴቶች ለመገንባት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጉባኤው ለጀመራቸው የሰላም ግንባታ ሰራዎች መቃናት ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የጋምቤላ፣ አሶሳ ፣ ቄለም፣ ምዕራብ ወለጋና ደቡብ ሱዳን አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል በበኩላቸው በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከእምነትና ሌሎች ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ሲከሰቱ በነበሩ ግጭቶች በሰው ህይወትና እምነት ተቋማት ላይ ጉዳት ሲደርስ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ሆኖም  በጋምቤላ ክልል ህዝቡ ባለው ተቻችሎ የመኖር መልካም እሴት ችግሮች አለመከሰታቸውን ጠቁመው ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የክልሉን መልካም አርያነት ለማስቀጠል እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የኃይማኖት ተቋማት ለክልሉ ብሎም ለሀገር የሰላም ግንባታ የማይተካ ሚና እንዳለቸው የተናገሩት ደግሞ  የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ኡጁሉ ኡጁሉ ናቸው።

በሀገሪቱ የተጀመረውን  የለውጥ ጉዞ ለማደናቀፍ  ለሚሞክሩ  ፀረ- ሰላም ኃይሎች ወጣቱ የጥፋት መሳሪያ እንዳይሆን የኃይማኖት አባቶችና ሀገረ ሽማግሌዎች የሰላም ግንባታ ሚናቸውን እንዲያጠናክሩ  ጠይቀዋል።

በኢትዮጰያ ንግድ ባንክ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ መሰለ ኃይሉ ባንኩ ሀገራዊ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በኢኮኖሚ ፣ በስራ እድል ፈጠራ፣ በጤና ሌሎችም ዘርፎች የበኩሉን ሚና ሲወጣ መቆየቱን አውስተዋል።

በአሁኑ ወቅትም በሀገራዊ የሰላም ግንባታ ውስጥ የድርሻውን ለመወጣት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው የአሁኑ  መረሃ ግብርም የዚሁ አንዱ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

ከትናንት ጀምሮ ዛሬም ቀጥሎ ባለው የውይይት መድረክ የኃይማኖት ተቋማት ተወካዮች ፣የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም