በዜጎች ውስጥ ሆነው የሚያጠፉትን መለየት ውስብስብ በመሆኑ ፖሊስ ራሱን ማብቃት አለበት

56

አዲስ አበባ  መስከረም 20/2013 (ኢዜአ) በዜጎች ውስጥ ሆነው የሚያጠፉትን የመለየት ተግባር ውስብስብ በመሆኑ ፖሊስ ራሱን ማብቃት እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሳሰቡ። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ''ከራስ በላይ ለህዝብና ለሃገር'' በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ባለው የፌዴራል ፖሊስ አመታዊ ክብረ በዓል ላይ ተገኝተው የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።

በስነ ስርዓቱ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጀኔራል ኮሚሽነር እንዳሻው ጣሰው፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወይዘሮ መአዛ አሸናፊና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና አምባሳደሮች ታድመዋል።

በሰጡት መመሪያ እንደገለጹት፤ ፖሊስ መጥፎ ዜጎችን ከሰላማዊ ዜጎች የመጠበቁ ስራ ልክ እንደተለየ ጠላት ተኩሶ የሚገድል ወይም ምሽግ ቆፍሮ የሚከላከለው አይደለም።

በህዝብ ውስጥ ሆነው እያጠፉ ያሉትን የመለየት ስራ እጅግ ውስብስብ መሆኑን አመልክተዋል።

በመሆኑም ይህንን ውስብስብ ሁኔታ ለመወጣት የፖሊስ ሰራዊት ራሱን ማብቃት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በተለይም በህግ፣ በስነ-ልቦና፣ በቴክኖሎጂ በሌሎች የዕውቀት ዘርፎች ራስን ማብቃት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሰራዊቱ ዛሬ ባሳየው ትርኢት በእጅጉ መኩራታቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፤ ሰራዊቱ ራሱን በማብቃት ለኢትዮጵያ ኩራት እንዲሆን የአደራ መልዕክት አስተላልፈዋል።

''ይህ ራስን የማብቃት የወትሮ ዝግጁነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ኢትዮጵያችን ለማንም ጠላት ሸብረክ ሳትል የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ አጠናክራ እንድትቀጥል ለራሱ ኩራት ለአካባቢ አገሮች ደግሞ የብቃት ምንጭ የሆነ ሰራዊት የመገንባት ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጣለሁ'' ብለዋል።

የቀረበው ትርኢት ሰራዊቱ አገር ወዳድ፣ ህዝብ አክባሪ፣ ቅንና ለአገሩ ታማኝ መሆኑን የሚያመለክት መሆኑን ገልጸዋል።

''በተለይም ራሱን ለአገሩና ለህዝቡ አሳልፎ የሚሰጥና ከሚመጣውና ከሚሄደው ጋር የሚሄድ ሳይሆን ሁሌም ከኢትዮጵያ መገለጫ ባንዲራ ጋር የሚዘምት እንደሆነ ለማሳየት እየተደረገ ያለውን ጥረት መሳካቱን የሚያመለክት ትርኢት የታየበት ነው'' ብለዋል።

ትርኢቱ በአገር ላይ የሚቃጣ ማንኛውንም ተልእኮ ለመመከት የሚያስችል መሆኑን የተመላከተበት እንደሆነ ነው ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም