የሐረሪ ክልል የብልጽግና ፓርቲ አመራሮችና አባላት ስልጠና ተጀመረ

57

ሐረር መስከረም 19/2013(ኢዜአ) የሐረሪ ክልል የብልፅግና ፓርቲ የመጀመሪያ ደረጃ አመራሮችና አባላት የተሳተፉበት የአቅም ግንባታ ሰልጠና ዛሬ በተለያዩ አዳራሾች ተጀመረ። 

በስልጠናው ቁጥራቸው ከ2ሺ300 በላይ የፓርቲው አመራሮችና አባላት እየተሳተፉ ነው።

የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱልጀባር መሐመድ በስልጠናው መድረክ እንደገለጹት ፓርቲው ለሀገሪቱ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና ልማት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።

ስልጠናውም አመራሮችና አባላት  ነባራዊ ሁኔታን በአግባቡ በመገንዘብ የሚያጋጥሙ  ችግሮችን ተቋቁመው  እንዲሰሩ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ የመጀመሪያ ደረጃ አመራሮችና አባላት   ህዝብ የሚያነሳቸውን መልካም አስተዳደር ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ስልጠናው ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።

ሰልጣኞችም በቆይታቸው  ያገኙትን  ክህሎት ወደ ታችኛው ማህበረሰብ በማውረድ የህዝቡ  የፍትህ ፣ መልካም አስተዳደርና ልማት ጥያቄዎችን በስራ በመመለስ  ማሳየት እንደሚጠበቅባቸው አስታውቀዋል።

የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ምክትል ኃላፊ አቶአብዱልሃኪም ኡመር  በበኩላቸው  ስልጠናው መሰረታዊ  የድርጅት አመራሮችን በተሻለ ሁኔታ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲሁም ስለ ብልፅግና ፓርቲ ዓላማ  በአግባቡ ተረድተው  ፕሮግራሙን ከማሳካት አንፃርም የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረውም አስረድተዋል፡፡

የብልጽግና እሳቤዎችን አመራሩ በአስተሳሰብና ተግባር እንዲሁም ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች አንድነት ፈጥሮ እንዲንቀሳቀስ ያስችላቸዋል ብለዋል።

አመራሮቹ ወደ ታች ወርደውም የማህበረሰቡን ንቃተ ህሊና ከማዳበርና የህዝቡን ጥያቄ ከመመለስ አንፃር እገዛ እንደሚያደርግ አብራርተዋል።

"ወቅታዊ ሁኔታዎችን መሻገሪያ ትልሞች" በሚል መሪ ሀሳብ በክልሉ ከተማና ገጠር በሚገኙ 13 የመሰብሰቢያ አዳራሾች የተዘጋጀው የአቀም ግንባታ ስልጠናው   ለሶስት ቀናት የሚቆይ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም