በኢትዮጵያ ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በልብ ሕመም ተጠቅተዋል

62

አዲስ አበባ መስከረም 19/2013(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በልብ ሕመም መጠቃታቸውን አንድ ጥናት አመለከተ።

ዓለም አቀፍ የልብ ቀን በልብ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ዛሬ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡

 የዓለም የልብ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ20ኛ ጊዜ የተከበረው  “ልባም በመሆን የልብ ነክ በሽታዎችን እንግታ “ በሚል መሪ ሀሳብ ነው፡፡

በበዓሉ ላይ የተገኙት የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ የኢትዮጵያ ጤና ሳይንስ ኢኒስቲትዩት እ.አ.አ በ2017 ዓ.ም ያስጠናውን ጥናት ጠቅሰው እንደገለጹት፣ በአገራችን ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የልብ ሕሙማን ናቸው፡፡

በመሆኑም "ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለልባችን ጤና መጠበቅ ልባሞች ሆነን መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል" ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ከፍተኛ የጤና ቀውስ እያስከተሉ እንደሚገኙና ከነዚህ ውስጥ የልብ ሕመም በግንባር ቀደምነት ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከልብ ጋር ለተያያዙ በሽታዎች ዋነኛ አጋላጭ ከሆኑ መንስኤዎች መካከል ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ በተለይ የጨው፣ ስኳርና መሰል አጠቃቀም እንዲሁም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግና ትንባሆ እንደሚጠቀሱ ሚኒስተሯ ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስትርም በሽታውን ለመከላከል የሚያግዙ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው፣ በተለይ ትምባሆ ላይ ከፍተኛ ታክስ እዲጨመር በማድረግ በትምባሆ አማካይነት ለልብ ሕመም የሚዳረጉ ዜጎችን ለመቀነስ ጥረት መደረጉን አመልክተዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ የደም ግፊት በሽታዎች ቅድመ ምርመራን በማስፋት በሽታው የታየባቸው ዜጎች በቶሎ ሕክምና እንዲገኙ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ዶክተር ሊያ አብራርተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በመንግስትና በግል ጤና ተቋማት በከፍተኛ የልብ ሕክምና ስፔሻሊስቶች ሕክምናው እየተሰጠ መሆኑንና አገልግሎቱን በየጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የማስፋፋት ሥራ መጀመሩንም አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልብ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ሄለን በፍቃዱ በበኩላቸው በዓሉን በዓመት አንዴ በማክበር ግንዛቤ የመፍጠር ሂደቱ ውጤታማ እንደማይሆን ገልጸዋል።

"በመሆኑም ከመጪው ጥቅምት ወር ጀምሮ ማዕከሉ ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ወር በገባ በመጨረሻው አርብ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ይሰራል" ብለዋል፡፡

ማዕከሉ ባለፉት አሥር ዓመታት ከ5 ሺህ 800 በላይ ለሆኑ ሕሙማን የልብ ቀዶ ሕክምና ማድረጉንና ከነዚህ ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት ህጻናት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

"በማዕከሉ በተገኘ መረጃም ከ7 ሺህ 600 በላይ ታካሚዎች የልብ ቀዶ ሕክምና ለማግኘት ወረፋ እየጠበቁ ይገኛሉ" በማለትም የችግሩን ስፋት ጠቅሰዋል።

ይህን ሰፊ ሥራ ማዕከሉ ብቻውን የሚወጣ ባለመሆኑ መንግስትም ሆነ ህብረተሰቡ የልብ ህሙማንን ለማገዝ ከእዚህ ቀደሙ በበለጠ ሰፊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው ሠራተኛው በሥራ ቦታ ላይ የሚያሳልፈው ጊዜ ሰፋ ያለ በመሆኑ ይህን ተከትሎ ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎችን ለመከላከል ከአጋሮች ጋር በመሆን እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

በተለይ ከዕድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ የሚመጣውን የልብ ሕመም ለመከላከል ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ እንደሚሰራ ዶክተር ኤርጎጌ አስታውቀዋል፡፡  

በበዓሉ ላይ የልብ ሕመምን የሚያሳይ የፎቶ ግራፍ አውደርዕይ እና ጥናታዊ ጹሁፍ ቀርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም