የኢትዮጵያ የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ለከፍተኛ የውሃ ብክለትና ብክነት ተጋልጠዋል ተባለ

130

አዲስ አበባ  መስከረም 19/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ለከፍተኛ የውሃ ብክለትና ብክነት መጋለጣቸው ተነገረ።

የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስ የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ በባለድርሻ አካላት ውይይት እየተካሄደበት ነው።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የውሃ ምህንድስና ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ቴድሮስ አሰፋ ለኢዜአ እንዳሉት በኢትዮጵያ ከ30 እና 40 ዓመት በፊት ጥራት ያላቸው የውሃ አካላት አሁን በከፍተኛ ደረጃ እየተበከሉ ነው።

ይህም የአካባቢ ስነ-ምህዳርና ብዝሃ ህይወትን በማዛባት ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው።

በተለይ በስምጥ ሸለቆ ሐይቆች አካባቢ ዘላቂ የተፋሰስ ልማት ስራ አለመሰራቱ ችግሩን እያባባሰው መሆኑን አንስተዋል።

የከተሞችና የኢንዱስትሪ መስፋፋት ደግሞ ለብክለቱ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ይላሉ።

እንደ ዶክተር ቴድሮስ ገለጻ ብክለቱን ለመቀነስ በተለይ የኢንዱስትሪ ዩኒቨርሲቲ ትስስር ላይ የተሻለ ስራ መሰራት አለበት።

ከብክለት ነጻ ኢንቨስትመንት መሳብና የብክለት ክትትልና ቁጥጥሩን ማጠናከርም አንዱ የመፍትሄ አካል መሆኑን ያነሳሉ።

የተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዳነች ያሬድ በበኩላቸው በስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ላይ ከመጠን ያለፈ የውሃ አጠቃቀም በመኖሩ ሐይቆች እንዲደርቁና እንዲጠፋ እያደረገ ነው ይላሉ።

በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በተፈጥሮ የሚከሰቱ ድርቅና ጎርፍ የመሳሰሉ ችግሮችም የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተግዳሮች መሆናቸውን አንስተዋል።

እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት የውሃ ሃብቱን በዘላቂነት ለመጠቀም በዘርፉ መሪ ዕቅድ የተቀመጡ የመፍትሄ ሀሳቦች መኖራቸውን አውስተዋል።

ለአስር ዓመቱ የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስ ልማት መሪ ዕቅድ 100 ቢሊዮን ብር ያህል በጀት እንደሚያስፈልግም ነው የተነገረው።

በኢትዮጵያ ከሚገኙ ዋና ዋና የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ሀዋሳ፣ አባያና ጫሞ፣ አቢጃታ ሻላ ይጠቀሳሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም