መጪውን ዘመን የሚመጥን የፖሊስ ሠራዊት ግንባታ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል

67

አዲስ አበባ  መስከረም 19/2013 ( ኢዜአ) መጪው ዘመን የሚመጥን የፖሊስ ሠራዊት ግንባታ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለፁ።

ራሱን የቻለ የፖሊስ ዶክትሪን ወይንም ፍልስፍና እየተዘጋጀ ሰለመሆኑም ተመላክቷል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን " ከራስ በላይ ለሀገርና ለህዝብ! " በሚል መሪ ቃል ነገ የሚያከብረውን በዓል አስመልክቶ ዛሬ በሸራተን አዲስ ሆቴል የፓናል ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጨምሮ፣ ሚኒስትሮች፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች፣ አምባሳደሮች፣ የፖሊስ ሠራዊት አባላትና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንገዶች ተገኝተዋል።

በመድረኩ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ አስካሁን ድረስ የተጓዘበትን ሂደት የሚዳስስ ዶክመንተሪ ፊልም ለታዳሚዎች ቀርቧል።

በተጨማሪም ፖሊስ ኮሚሽኑ በተቋም ግንባታና በሪፎርሙ እየሰራቸው ያሉ አጠቃላይ ሥራዎች በተመለከተ ለፓናል ውይይቱ መነሻ ሀሳብ ቀርቦ በተሳታፊዎች አስተያየት ተሰጥቶበታል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽ ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት የፖሊስ ተልዕኮ ከጊዜ ወደጊዜ እየከበደና በውስጥም በውጭም በርካታ ፈተናዎች እየገጠሙት መሆኑን አንስተዋል።

በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከአገራዊ ለውጡ ጋር በተያያዘ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች እየገጠሙት መሆናቸውን ጠቅሰው፣ እነዚህን ችግሮች መፍታት በሚያስችል መልኩ ተቋሙን የመለወጥ ሥራ በጥናት ተካሂዶ በአሁኑ ወቅትም የለውጥ ሥራው መጠናከሩን ገልጸዋል።

በዚህም በአደራጃጀት፣ በሰው ኃይል፣ በግብዐት አቅርቦት፣ በቴክኖሎጂና በመሳሰሉት ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮች እየተፈቱ ተጨባጭ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆናቸውን ነው ያስረዱት።

የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎችን ለማስቀጠልና የህግ የበላይነት በዘላቂነት ለማስከበር በተሻለ ሁኔታ እንደሚሰራም ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው አረጋግጠዋል።

የክልል መንግስታት ለዚህ የሚመጥን የሰው ኃይል ግንባታ ሥራ ላይ የድርሻችውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው፣ በሪፎርሙ ፖሊስ አንድን ስርዓት እንዲያገለግል ሳይሆን ቀጣይነት ያለው ህዝብና አገርን የሚያገለግል ተቋም እንዲሆን ተደርጎ መደራጀቱን ተናግረዋል።

ፖሊስ ውስጥ የተደረገው ለውጥ መጠነ ሰፊ እና በህዝብ ውስጥ የሚኖረውን እምነት የሚጨምር መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ ''ፖሊስ ተፈርቶ የሚከበር ሳይሆን ተወዶ የሚከበር'' መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

ሁለንተናዊ ደህንነት የመጠበቅና አገልግሎት ሰጪነቱን በውጤታማነት ለመፈጸም የሚያስችል መጠነ ሰፊ የለውጥ ሥራዎችን እየሰራ ሰለመሆኑም ገልፀዋል።

ራሱን የቻለ የፖሊስ ዶክትሪን ወይንም ፍልስፍና እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመው በእዚህም የፖሊስ አደረጃጀት ምን መሆን አለበት የሚለው ጥያቄ በእዚያው ምላሽ እያገኘ እንደሚሄድ ተናግረዋል።

በመጨረሻም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ለሠራዊቱ አባላት ባስተላለፉት መልዕክትና በሰጡት የሥራ መመሪያ ዘመናዊ ፖሊስ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ በርካታና ጠንካራ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን አንስተዋል።

ይሁን እንጂ ጥቂት አገርንና ወገንን የበደሉ መታረም ያለባቸው ክስተቶች እንደነበሩ አስታውሰው ፣ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ አንፃር በሪፎርሙ ትኩረት የተሰጠው አንዱ ፖሊስ በመሆኑ እነዚህ ጉዳዮች እየታረሙ መምጣታቸውን ገልፀዋል።

ፖሊስ ፈርሶ የሚገነባ ሳይሆን ከቀደሙት ዘመናት የሚጠቅሙ ቁም ነገሮችን በመውሰድ ዘመን ተሻጋሪ ተቋም የሚገነባ መሆኑንም አመልክተዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተከናወኑ ሥራዎች ፖሊስ ወደ አንድ የለውጥ ምዕራፍ መሸጋገሩን አቶ ደመቀ ተናግረዋል።

ፖሊስን ማዘመንና ተሻጋሪ እንዲሆን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ እውን እንዲሆን ህብረተሰቡ፣ መንግስት እና ፖሊስ በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

መንግስት ከዚህ አንፃር ያለበትን ኃላፊነት በአግባቡ እንደሚወጣ ገልጸው፣ ለመጪው ዘመን የሚመጥን የፖሊስ ሠራዊት ግንባታ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በአጽንኦት ተናግረዋል::

በ1934 ዓ.ም በዘመናዊ መልክ የተደራጀው የኢትዮጵያ ፖሊሰ ሠራዊት ከጊዜ ወደ ጊዜ በአገልግሎትም ሆነ በአሰራር ራሱን እያዘመነ አሁን ካለበት ደረጃ መድረሱን በመድረኩ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም