የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት በዘርፉ የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ላይ ከአጋር አካላት ጋር ተወያየ

119

አዲስ አበባ መስከረም 19/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ባዘጋጀው የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ላይ ከአጋር አካላት ጋር ተወያየ።

መሪ ዕቅዱ ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን ዓለም አዓቀፍ ስምምነቶች ተቋማት እንዲተገበሩ ለማድረግ የሚረዳ መሆኑም ተገልጿል።

የቅንጅቱ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሳባ ገብረመድህን መንግስት የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በተለይ ለሴቶች የገንዘብ ብድርና ቁጠባ አገልግሎት በመስጠት ወደሥራ እንዲገቡና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲያሳድጉ እየሰራ ያለው ሥራ የተሻለ መሆኑን በዚሁ ወቅት ጠቁመዋል፡፡

በዘርፉ የተዘጋጀው የአሥር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድም ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች ተቋማት በአግባቡ እንዲተገብሩ ለማድረግ የሚረዳ መሆኑንም አመልክተዋል።

የውይይት መድረኩም በመሪ ዕቅዱ ላይ የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ ካለው ጠቀሜታ በተጨማሪ በአፈጻጸም ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለይቶ በማውጣት መፍትሄ ለማቅረብ የሚያገዝ መሆኑን ተናግረዋል ።

የቅንጅቱ አማካሪ ወይዘሪት ራሔል ተሰማ ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት የተለያዩ ተቋማት ህጻናት እና ሴቶችን ተደራሽ ለማድረግ በዕቅዳቸው እንዲያካትቱ የሚያደርግ አሰራር በዕቅዱ እንዲካተት ሀሳብ መስጠታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች ተቋማት ምን ያህል ይተገብራሉ የሚለውን የሚፈትሽና የማስፈጸም አቅማቸውንም ለመገምገም የሚረዳ አሰራር እንዲዘረጋ ማሳሰባቸውንም አመላክተዋል።

በውይይቱ የተሳተፉት የ"ሴቶች ይችላሉ ማህበር" መስራችና ዳይሬክተር ወይዘሮ የምወድሽ በቀለ በበኩላቸው "የአሥር ዓመት መሪ ዕቅድ ላይ የሴቶች ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠው እና በውሳኔ አሰጣጥ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በቀጣይ ለመፍታት በጋራ ውይይት መደረጉ አስፈላጊ ነው" ብለዋል።

የዛሬ ሁለት ዓመት 50 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ወደ አመራር ሰጭነት እንዲመጡ መደረጉን አስታውሰው ሴቶች ከያዙት ኃላፊነት ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ሲነሱና በወንዶች ሲተኩ እንደሚታይም ተናግረዋል።

የዚህ ምክንያት ደግሞ ሴቶችን ወክሎ ተጠያቂ የሚያደርግ ተቋም አለመኖሩና ይህም እንደ ክፍተት የሚታይ መሆኑን ነው አመልክተዋል።

"የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ የታጨቀ ኃላፊነትን በመያዙ ሴቶችን እኩል የማድረጉ ተግባር አዝጋሚ እንዲሆን አድርጎታልም" ብለዋል ወይዘሮ የምወድሽ።

እንደእሳቸው ገለጻ በዘርፉ የሚሰሩ አካላት በአሥር ዓመት መሪ ዕቅድ ላይ ውይይት ማድረጋቸው ክፍተቶች መፍትሄ እንዲያገኙ እና የመዋቅር ችግሮችን ፈትሾ ምላሽ ለመስጠት ይረዳል።

"በተለይ በሴቶች መብት ላይ የምንሰራ አካላትን በጉዳዩ ላይ ማነጋገሩ ለመፍትሄ ቅርብ ስለሚያደርግ መድረኩ መዘጋጀቱ መልካም ነው '' ያሉት ደግሞ የአማራ ሴቶች ማህበር ዋና ጸሐፊ ወይዘሮ ትጥቅነሽ አለሙ ናቸው ።

ውይይቱ ክፍተቶችን በመለየትና ለመንግስት በማሳየት ልማቱን የጋራ በማድረግ ወደ እድገት ለማምጣት ይረዳል ሲሉም ነው የገለጹት።

መሪ ዕቅዱ ተቋማት የሴቶችን ጉዳይ እንዴት አካተው መስራት  እና ተጠቃሚነታቸው ላይ ማተኮር አለባቸው የሚለውን በትኩረት መመልከቱን ወይዘሮ ትጥቅነሽ በአዎንታዊነት አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር  ከ2003 ጀምሮ በሴቶች እኩልነትና ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ  እየሰራ መሆኑ ተገልጿል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም