በቂ ዝግጅት ያላደረጉ ትምህርት ቤቶች መማር ማስተማር አይጀምሩም -- ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

71

አዲስ አበባ መስከረም 19/2013(ኢዜአ) በቂ ዝግጅት ባልተደረገባቸው ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ስራ እንደማይጀመር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ። 

ከዚህ አንጻር በየደረጃው ያሉ የፖለቲካ አመራሮች ትምህርት ቤቶች የሚያደርጉትን ዝግጅት በልዩ ሁኔታ እንዲደግፉና እንዲያስተባብሩ ነው ጥሪ ያቀረቡት።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትምህርት ቤቶችን ዝግጅት በሚመለከት ከክልል ትምህርት ቢሮ አመራሮችና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች ጋር በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ተወያይተዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ትምህርት ቤቶች አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገው ወደ መማር ማስተማር እንዲገቡ የሁሉንም አካል እገዛ እንደሚሹ ተናግረዋል።

ከፌዴራል ተቋማት እስከ ትምህርት ቤቶች ደረስ የሚዘልቅ አደረጃጀት ተዋቅሮ ወደ ስራ እንደሚገባም አብራርተዋል።

የሚዋቀሩት አደረጃጀቶች መረጃ የሚለዋወጡበት አሰራር እንደሚዘረጋም እንዲሁ።

አደረጃጀቶቹ ትምህርት ከማስጀመር በተጨማሪ በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ አስፈላጊ የጥንቃቄ ምክረ ሃሳቦች እንዲተገበሩ ክትትል እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ሁርካቶ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት ለማስጀመር ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆንን ጠቁመዋል።

ግብረ ሃይሉ ከነገ ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ዩኒቨርሲቲዎች እያደረጉ ያሉትን ዝግጅት የመስክ ምልከታ እንደሚያካሄድ ነው ያስረዱት።

"በመስክ ምልከታው በቂ ዝግጅት እንዳደረጉ በተለዩ ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ የመማር ማስተማር ስራውን እንጀምራለን" ብለዋል።

ከኮሮና ቫይረስ ጥንቃቄዎች ባሻገር በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሁኔታ እንዲኖር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ትምህርት ቤቶችን በዚህ ቀን እንከፍታለን ከሚለው ቀነ ቀጠሮ ይልቅ ለዝግጅት ስራዎች ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል።

በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚኖሩ ማህበረሰቦች የዝግጅት ምዕራፉ ዋነኛ ተሳታፊ መሆን እንዳለባቸው ጠቁመው "ለሁሉም ነገር መፍትሄውን ከአንድ ቦታ መጠበቅ ተገቢ አይደለም" ብለዋል።

በመሆኑም በዝግጅት ወቅት ለሚገጥሙ ችግሮች አካባቢያዊ መፍትሄዎችን ማበጀት ላይ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

በቂና አስተማማኝ ዝግጅት ባላደረጉ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ስራ እንደማይጀመርም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

ከዚህ አንጻር በየደረጃው የሚገኙ የፖለቲካ አመራሮች ትምህርት ቤቶች የሚያደርጉትን ዝግጅት በልዩ ሁኔታ እንዲደግፉና እንዲያስተባብሩ ነው ጥሪ ያቀረቡት።

የተለያዩ ምክንያቶችን እያስቀመጡ ትምህርት ቤቶች በቂ ዝግጅት እንዳያደርጉ በቸልተኝነት በሚሰሩ አመራሮች ላይ አስፈላጊው የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድም ጨምረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም