የፖለቲካ ፓርቲዎች ፀረ ህገ መንግስት እንቅስቃሴ የሚያራምዱ አካላትን እንዲታገሉ ጥሪ ቀረበ

84

ሀዋሳ መስከረም 19/2013 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፀረ ህገ መንግስት እንቅስቃሴ የሚያራምዱ አካላትን ነቅተው በመጠበቅ እንዲታገሉ ጥሪ ቀረበ። 

በደቡብ ክልል የሚንቀሳቀሱ ብልጽግናን ጨምሮ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሳተፉበት የሠላም ምክክር መድረክ  ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተካሄዳል።

የክልሉን ብልጽግና ፓርቲ የሚመራው የደቡብ ክልላዊ  መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው በመድረኩ   የፖለቲካ ፓርቲዎችና መንግስት ተቀራርበን  ከሰራን ሠላማችንን ማፅናት እንችላለን ብለዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ በየአካባቢው የተለያየ የሰላም ማደፍረስ ለመፍጠር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችና ሴራዎች እንዳልቆሙ ተናግረዋል።

በተለይ ከህግ ባፈነገጠ መንገድ የፖለቲካ ፍላጎትን ለማሳካት በሚንቀሳቀሱ አካላት ህዝቡ  ያልተፈለገ ዋጋ እየከፈለ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ያልተመለሱ የህዝብ ጥያቄዎች በህግና ሥርዓት የሚመለስበትን ሁኔታ ከመፍጠር ይልቅ በግጭት እንዲፈቱ የሚደረጉ ሴራዎችን በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲታገሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ማናቸውንም ጥያቄዎች በኃይልና ጉልበት እንዲፈቱ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ዋጋ እንደሚያስከፍሉ በማስገንዘብ  ፓርቲዎቹ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም አመልክተዋል።

አንዳንዶች ህገ መንግስቱን በግላጭ የሚንድ አስተሳሰብ ይዘው የሚያራምዱት አካሄድ በምንም መመዘኛ ተቀባይነት እንደሌለውም አቶ ርስቱ አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ ያለውን አንፃራዊ ሠላም ዘላቂነቱንና ደህንነቱን ለማረጋገጥ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመመክር ታስቦ የፎረሙ መድረክ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።  

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የዶንጋ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጸሐፊ አቶ ተሰማ ለመንጎ በሰጡት አስተያየት መድረኩ በቀጣይ በሰላምና በሃገር ጉዳይ ላይ ተመካክሮ ለመስራት የሚያበቃ መሆኑን ገልጸዋል።

የጌዴኦ ህዝብ ዴሞክራሲ ድርጅት ሊቀመንበር አቶ አለሣ መንገሻ በበኩላቸው መድረኩ በሃገሪቱና ህዝቦች  ጉዳይ ለመምከር የቻሉበት በመሆኑ መርካታቸውን ገልጸው መሰል መድረኮች እስከታችኛው መዋቅር መዘጋጀት እንዳለበትም አመልክተዋል።

በመድረኩ  የተሳተፉ  ፓርቲዎች   በቆይታቸው በክልሉ ሰላምና ደህንነት ሁኔታ የመከሩ ሲሆን በቅርቡ  የመንግስትና ፓርቲዎች የጋራ ፎረም ለመመስረት ሶስት አባላት ያሉት ኮሚቴ  በማዋቀር መረሃ ግብራቸውን አጠናቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም