የአየር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ ከጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር የቅየሳ አውሮፕላን በረራ አገልግሎት ለመጀመር ተስማማ

80

አዲስ አበባ  መስከረም 19/2013 ( ኢዜአ) የአየር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ ከጂኦስፓሻያል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር የቅየሳ አውሮፕላን በረራ አገልግሎት ለመጀመር የሚያስችል ስምምነት አደረጉ። 

ስምምነቱ የአገሪቷን ሁለንተናዊ ልማትና እድገት ለማረጋገጥ የሚያስፈልጉ መሰረታዊ የመረጃ አቅርቦትና ተደራሽነትን ለማስፋት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ይረዳል ተብሏል።

የየግብርናውን ኢኮኖሚ ለማሳደግ እንዲሁም የከተማ ልማትና እቅድ ስራዎችን በማቀላጠፍ ለማሳካት እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል።

በቂ መሰረተ ልማት ከመገንባት አኳያም አገራዊ የመረጃ ማሰባሰብ አቅም ተፈጥሮ በተለይም የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ምርታማነትና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ሰፊ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።

የኢትዮጵያ ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቱሉ በሻ እንደገለጹት በሁሉም አካባቢ የመረጃ አቅርቦትና ተደራሽነትን በበቂ ሁኔታ ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

በመሆኑም በአየር በረራ በመታገዝ በኢትዮጵያ መሰረታዊ መረጃዎችን የመሰብሰብ ስራ በተጠናከረ ሁኔታ ለማካሄድ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም ሲሰራ የቆየው የአየር ፎቶግራፍ መረጃ የማሰባሰብ ስራም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ይህንንም በተለይ በቂ የመረጃ ሽፋን በሌለባቸው ክልሎችና አካባቢዎች ለማድረስ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።  

እንደ ዶክተር ቱሉ ገለጻ በቀጣይም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በተለይ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ለማፋጠን የሚያስችሉ ስራዎችን ለመስራት ታቅዷል።

የመረጃ አቅርቦትን ለማሳደግና የአገሪቷን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማረጋገጥ ብሎም ብሔራዊ ደህንነትን ለማስጠበቅ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በስምምነቱ መሰረትም ከአየር ኃይል ጋር በመሆን ሁለት ዘመናዊ አውሮፕላኖችን መረጃ ለማሰባሰብ በሚያስፈልግበት በማንኛውን ጊዜ በመጠቀም መረጃዎችን በፍጥነት የማሰባሰብ ስራ ይሰራል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማጎልበትና መረጃ ለማሰባሰብ ለሚያስፈልጉ ጉዳዮች አውሮፕላኖች ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ተቋሙን ለመደገፍና ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ እንዲሁም ከአገር ውስጥ አልፎ በውጭ አገር ጭምር በመስራት የውጭ ምንዛሬን ለማስገኘት ይሰራል ብለዋል።

ከ2004 እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ ብቻ በአገር አቀፍ ደረጃ 46 በመቶ የአየር ፎቶግራፍ መረጃ የተሰበሰበ መሆኑን ከኢትዮጵያ ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም