የሚጠበቅባቸውን ውዝፍ ግብር ባልከፈሉ ግብር ከፋዮች ላይ እርምጃ ሊወሰድ ነው

162

መቀሌ/ጅማ/ መስከረም 19/2013 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል የሚጠበቅባቸውን ውዝፍ ግብር ባልከፈሉ የፌደራል ግብር ከፋዮች ላይ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱን በገቢዎች ሚኒስቴር የመቀሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጅማ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽህፈት ቤት  በበኩሉ  በተያዘው የበጀት ዓመት ካለፈው የስራ ዘመን በ62 ሚሊዮን ብር ብልጫ ያለው የግብር ገቢ ለመሰብሰብ ማቀዱን ገልጿል።

በገቢዎች ሚኒስቴር የመቀሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ተክላይ አብርሃ ለኢዜአ እንዳሉት በተያዘው የበጀት ዓመት በክልሉ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ያልተከፈለ 136 ሚሊዮን ብር የግብር ውዝፍ እዳ ለመሰብሰብ  እየተንቀሳቀሱ  ነው።

በኮሮና ምክንያት ከ2008 ዓ.ም በፊት ውዝፍ የግብር እዳ የነበረባቸው ግብር ከፋዮች የፌዴራል መንግስት  ባፃደቀው የግብር የምህረት አዋጅ መሰረት ነፃ መሆናቸውን አስታውሰዋል።

ከ2008 ዓም እስከ 2011 ዓ.ም ውዝፍ ግብር ያለባቸው  በአንድ ጊዜ ለሚከፍሉ መንግስት የ10 በመቶ ቅናሽ ማድረጉ ጠቅሰው ፤ ይህም ግብር ከፋዩን ለማበረታት መሆኑን  አስረድተዋል።

መንግስት ባወጣው የግብር አከፋፈል ስርዓት ከወለድና ቅጣት ነፃ ይሆናሉ ተብለው ባለፈው ዓመት ከተለዩ 133  ግብር ከፋዮች  ውስጥ ተጠቃሚ የሆኑት 86  ብቻ እንደሆኑ አመልክተዋል።

በተያዘው የበጀት ዓመት ውዝፍ ግብር ባለባቸው ከ40 የሚበልጡ  ግብር ከፋዮች በህጉ  መሰረት ንብረታቸውን እና የባንክ ሂሳባቸውን ለማገድ እንደሚገደዱ አስታውቀዋል።

ባለፈው ዓመት ከ101 ሚሊዮን ብር በላይ  ውዝፍ እዳ ግብር መሰብሰብ መቻሉን ስራ አስኪያጁ አውስተዋል።

ግብር ከፋዮቹ ታክስ ኦዲት ይፋ ከሆነ  በ30 ቀናት  ውስጥ ለመክፈል ዝግጁ ከሆኑ ከወለድና ቅጣት ነፃ እንደሚሆኑ የገለጹት አቶ ተክላይ፣ በተባለው ጊዜ ካልከፈሉ ግን የህግ  ማስከበር  ስራ ይሰራል "ብለዋል።

'የማነ እና ኃይለኪሮስ ጠቅላላ የንግድ ስራ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ምክትል ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ወልዱ ተስፋዬ በሰጡት አስተያየት ህግ በማክበርና ግልፅ አሰራር  በመከተል ግብር በአግባቡ እየከፈሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ባለፈው የበጀት ዓመት ብቻ ከ 9 ሚሊዮን  965 ሺህ ብር በላይ ግብር በመክፈል በፌዴራል ደረጃ የብር ተሸላሚ እንደነበረም  አስታውሰዋል።

በቀጣይ ጥቅምት ወር የሚጠበቅባቸውን  የ2012 ዓ.ም  ግብር  ለመክፈል መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል።

ቅርንጫፉ ባለፈው የበጀት ዓመት 2 ቢሊዮን 500 ሚሊዮን መሰብሰቡንና በተያዘው የስራ ዘመን ደግሞ ከተለያዩ የገቢ ምንጮች ከ2 ቢሊዮን 400 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ማቀዱ ተመልክቷል።

በሌላ በኩል የጅማ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽህፈት ቤት በተያዘው የበጀት ዓመት ካለፈው የስራ ዘመን በ62 ሚሊዮን ብር ብልጫ ያለው የግብር ገቢ ለመሰብሰብ ማቀዱን የጽህፈት ቤቱ  አቶ ተመስገን ገመቹ ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ ለመሰብሰብ የታቀደው  458 ሚሊዮን ብር እንደሆነ አስታውቀዋል።

በጽህፈት ቤቱ የገቢ ክትትል የስራ ሂደት ኃላፊ አቶ መሐመድ ሳኒ ከሊል በበኩላቸው የከተማውን ገቢ ለማሳደግ ሰራተኞች በመናበብና ቅንጅታዊ ውህደት ፈጥሮ መስራት አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

ለዚህም ከሰራተኞች ጋር  የጋራ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

የጅማ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽህፈት ቤት ከ100 በላይ  የሰው ኃይል እንዳለውም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም