በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት እየተሰራ ነው - የጤና ሚኒስቴር

109

አዲስ አበባ ፣መስከረም 19/2012 (ኢዜአ) በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት እንዳይስተጓጎልና የአገልግሎቱን ተደራሽነት ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊየ ታደሰ ገለጹ።

የጤና ሚኒስቴር የዓለም የቤተሰብ ዕቅድ ቀንን "መቆም የለም በኮቪድ-19 ጊዜ ለቤተሰብ ዕቅድ ፍላጎት ምላሽ እንስጥ” በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ አክብሯል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት በአገሪቷ የእናቶች ሞት እንዲቀንስና ጤናቸውም እንዲሻሻል የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ከፍተኛ ድርሻ አለው።

ያም ሆኖ አሁንም በየዓመቱ ከ11 እስከ 13 ሺህ የሚሆኑ እናቶች ከወሊድ ጋር በተያያዘ ለህልፈት እየተዳረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህ ደግሞ አሁንም አገልግሎቱን በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች በፍትሃዊነት ማዳረስ ባለመቻሉ መሆኑን ጠቁመው የእናቶች ጤና ትኩረት የሚሻ ነው ብለዋል።

ስለዚህም የቤተሰብ እቅድ ዘዴዎች ህይወትን የማዳን ተልዕኮ ያላቸው መሆኑን በመገንዘብ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ መሰራት እንዳለበት አመልክተዋል።

በተለይም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት አገልግሎቱን ለእናቶችና ለልጃገረዶች ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንና ለዚህም ሁሉም አካላት ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ደረጄ ድጉማ በበኩላቸው የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተደራሽነት ምንም እንኳን መሻሻሎች ቢያሳይም አሁንም መሰራት ያለበት ዘርፍ ነው ብለዋል።

ያም ሆኖ እ.አ.አ 2000 የቤተሰብ አገልግሎት አገራዊ ተደራሽነት 8 በመቶ መሆኑን አስታውሰው በ2019 አሃዙን ወደ 41 በመቶ ማድረስ መቻሉ ስኬት መሆኑን ጠቅሰዋል።

የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተደራሽነት በተለይም በከተሞች እመርታ ያሳየ መሆኑን ጠቁመው በገጠራማ እና በአርብቶ አደር አከባቢዎች አሁንም ተደራሽነት ላይ ይቀራል ነው ያሉት።

አገልግሎቱን ተደራሽና ፍትሃዊ ለማድረግ ሁሉም አካላት በሃላፊነት መንቀሳቀስ እንዳለባቸውና ወንዶች በዚህ ረገድ የሴቶች አጋር መሆን እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የዘንድሮው የዓለም የቤተሰብ እቅድ ቀን አዘጋጅ የሆነው የሶማሌ ክልል ዝቅተኛውን የክልሉን የአገልግሎት ተደራሽነት ይበልጥ ለማስፋት ላሳየው ቁርጠኝነት በመድረኩ ምስጋና ተችሮታል።

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ በመድረኩ ላይ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት ክልሉ በቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ዝቅተኛ አፈጻጸም እንዳለው ገልጸዋል።

በክልሉ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት አጠቃቀም 3 ነጥብ 4 በመቶ ሲሆን እናቶች በህይወት ዘመን የሚወልዱት አማካይ የልጆች ቁጥርም 7 ነጥብ 2 መሆኑን ተናግረዋል።

ያም ሆኖ ችግሩን ለማቃለል የክልሉ አስተዳደር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ነው አቶ ሙስጠፌ የገለጹት።

የቤተሰብ እቅድ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ13ኛ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለአምስተኛ ጊዜ ነው የተከበረው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም