በፀጥታ ችግር ንብረታቸውን ላጡ አሰሪዎች የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ይፋ ሆነ

75

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19/2013 ( ኢዜአ) በወቅታዊ የፀጥታ ችግር ምክንያት ንብረታቸው ለወደመባቸው አሰሪዎች የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ይፋ ተደርጓል፡፡

የድጋፍ ማሰባሰቢያው ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ በተነሳው ሁከት ለዓመታት ሰርተው ያፈሩት ሀብትና ንብረታቸው የወደመባቸውን አሰሪዎች መልሶ ማቋቋሚያ ነው ተብሏል።

"አሰሪው ለአሰሪው" የተሰኘው ይህ መርሃ ግብር የአገሪቷን የኢኮኖሚ እድገት ለማስቀጠል፣ ማኅበራዊ መረጋጋት ለመፍጠርና ስራ ፈጣሪዎችን መልሶ ለማቋቋም ያለመ መሆኑም ተገልጿል።

በቅርቡ በተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ሳቢያ ንብረታቸው ለወደመባቸው አሰሪዎች የገንዘብና የአይነት ድጋፍ የሚሰባሰብበትም ነው።

የመርሃ ግብሩ ግብ ግማሽ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ሃብት በገንዘብና በአይነት በማሰባሰብ ለተጎጂዎቹ በፍትሀዊነት በማከፋፈል ወደ ስራ መመለስና ተነሳሽነታቸውን ማነቃቃት እንደሆነም ተገልጿል።

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በተፈጠረው ችግር የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት በሆኑት አሰሪዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመጠገን የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብሩ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግረዋል።

ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት ዋነኛው መፍትሄ የስራ ዕድል መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ ፤ ለዚህ ደግሞ አሰሪዎች ቀዳሚ ባለድርሻ ናቸው ብለዋል።

በመሆኑም የደረሰባቸውን ጉዳት ለማቃለል ተባብሮና ተደጋግፎ መልሶ ወደ ነበሩበት ሁኔታ እንዲገቡ ማቋቋም የግድ ይላል ነው ያሉት።

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው ጉዳት የደረሰባቸውን አሰሪዎች መልሶ ለማቋቋም የክልሉ መንግስት የበኩሉን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።

ለሚፈጠሩ ችግሮች ዋነኛው መፍትሄ የሕግ የበላይነትን ማስከበር በመሆኑ መንግስት በዚህ ላይ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።

የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ ሕዳር 30 ቀን 2013 ዓ.ም የሚጠናቀቅ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም