ሃሰተኛ የብር ኖት ይዘው ተገኝተዋል ተብለው የተከሰሱ ግለሰቦች በእስራት እንዲቀጡ ተወሰነባቸው

59

ባህር ዳር፣ መስከረም 19/2013(ኢዜአ) በባህር ዳር ከተማ ሃሰተኛ አዲሱን ባለ አንድ መቶ የብር ኖት ይዘው ተገኝተዋል ተብለው የተከሰሱ ሁለት ግለሰቦች በእስራት እንዲቀጡ ተወሰነባቸው።

የባህር ዳርና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ በዋለው ችሎት እንደተመለከተው በባህር ዳር ከተማ የሚኖሩት እነዚህ ግለሰቦች ድርጊቱን የፈጸሙት መስከረም 15 እና 16 /2013 ዓ.ም  ነው።

አንደኛው ተከሳሽ ከ15 ሺህ ብር መካከል እና ሌላኛው ደግሞ ከሰባት ሺህ ብር ውስጥ አንዳንድ አዲሱን የባለ መቶ ሀሰተኛ የብር ኖቶችን ይዘው ባንክ ለማስገባት ሲሞክሩ በመገኘታቸው በቁጥጥር ስር ውለው እንደቆዩ ተገልጿል።

ተከሳሾቹ ወንጀሉን ሆን ብለው ያደረጉት እንኳ ባይሆን ሃሰተኛ የብር ኖት ይዘው እስከተገኙ ድረስ ጥፋተኛ መሆናቸውን በችሎቱ ተመልክቷል።

ግለሰቦቹ በቀረበባቸው ማስረጃ  ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ፍርድ ቤቱ ዛሬ በዋለው ችሎት እያንዳንዳቸው በአንድ ወር ቀላል እስራት እንዲቀጡ  መወሰኑን የችሎቱን ሂደት የተከታተለው ሪፖርተራችን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም