የታዳሽ ኃይል ትራንስፖርት ላይ የሚመክር መድረክ እየተካሄደ ነው

89

አዲስ አበባ መስከረም 19/2013 (ኢዜአ) የትራንስፖርት ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ትራንስፖርት ማስፋፋት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር ውይይት እያደረገ ነው።

በመድረኩ የታዳሽ ኃይል ትራንስፖርትን በኢትዮጵያ በማስተዋወቅ ምሣሌ የሆኑ ድርጅቶች ተሞክሯቸውን አቅርበዋል።

የትራንስፖርት ሚንስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በዚሁ ወቅት አንዳሉት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ያገለገሉ አነስተኛ ጥራት ያላቸው መኪኖች ከሚጠቀሙት ነዳጅ ጋር ተደምሮ በትራንስፖርት ዘርፉ የሚለቀቀውን ሙቀት አማቂ ጋዝ መጠን እንዲጨምር አድርጎታል።

ከትራንስፖርት ዘርፍ ከሚለቀቀው የሙቀት አማቂ ጋዝ መጠን 75 በመቶ የሚሆነው ከመንገድ ትራንስፖርት በተለይም ከጭነትና ከኮንስትራክሽን ተሽከርካሪዎች እንዲሁም ከግል ተሽከርካሪዎች የሚለቀቅ መሆኑንም በንግግራቸው ጠቁመዋል።

ከዚህ አንጻር ዘመናዊ፣ ተወዳዳሪና ተደራሽ የትራንስፖርት አገልግሎትን በተለየ ትኩረት መገንባት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት የራሱ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ገልጸዋል።

በታዳሽ ኃይል ትራንስፖርት ላይ በትኩረት የሚወያየው ይህ መድረክ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን በመድረኩም የተሽከርካሪ አምራቾች፣ ገጣጣሚዎችና አስመጪዎች ተገኝተዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎችም በዘርፉ ያሉ ምቹ ሁኔታዎችና ተግዳሮቶች ላይ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም