ኅብረተሰቡ የኢሬቻን በዓል በአባ ገዳዎች ኅብረት በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ማክበር አለበት

92

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19/2013 ( ኢዜአ) ኅብረተሰቡ የኢሬቻን በዓል ራሱንና ቤተሰቡን ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በመጠበቅ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት እንዲያከብር አባገዳዎች አሳሰቡ።

የኦሮሞ የአባገዳዎች ኅብረት መስከረም 23 ቀን 2013 በአዲስ አበባ የሚከበረውን የሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል አከባበር አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በውስን ሰው እንዲከበር መወሰናቸውን አባገዳዎቹ ተናግረዋል።

የኢሬቻ በዓል የሠላም፣ የፍቅርና የምስጋና በዓል ነው ያሉት አባ ገዳዎቹ ፤ መላው የኦሮሞ ወጣት በዓሉን ከፖለቲካ በጸዳ መንገድ እንዲያከብር ጥሪ አስተላልፈዋል።

በዓሉ እንደ ከዚህ ቀደሙ በሠላም እንዲከበር የበዓሉ ተሳታፊዎች የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

ኅብረተሰቡ የኮሮና ወረርሽኝን መከላከልን መሰረት ባደረገ መልኩ በዓሉን በየአካባቢው ማክበር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

'ከበዓሉ በላይ ቅድሚያ ለሰው ልጅ ህይወት መስጠት ስለሚያስፈልግ ጥንቃቄ እንዳይለያችሁ ሲሉ የኦሮሞ አባገዳዎች ኅብረት ጸሃፊ አባ ገዳ ጎበና ሆላ አሳስበዋል።

ይህ ሳምንት የሠላም በመሆኑ የተጣሉ የሚታረቁበት፣ የተቃቃሩ ይቅር የሚባባሉበት ነው በዚሁ መሰረት ሠላም ማውረድ ያስፈልጋል ብለዋል።

ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ እሴትና ባህል በመሆኑ ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ መከበር አለበት ብለዋል።
    

እንደ ወትሮው አንድ ላይ መሰባሰብ አስቸጋሪ መሆኑን በመግለጽ በዓሉን ሁሉም ሰው በያለበት ቦታ ሆኖ ማክበር ይችላል ነው ያሉት።

ኢሬቻ የአንድነትና የሠላም ተምሳሌት በመሆኑ ወጣቶችና ሌላውም ህብረተሰብ በዓሉ በሠላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም