አባገዳዎችና ወጣቶች በመስቀል በዓል የታየውን ሠላም በኢሬቻም ለመድገም እንሰራለን አሉ

54

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19/2013 ( ኢዜአ) የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አባገዳዎችና ወጣቶች በመስቀል በዓል የታየውን ሠላም በኢሬቻም ለመድገም እንደሚሰሩ ተናገሩ።

በአዲስ አበባ ለሁለተኛ ጊዜ የሚከበረው የዘንድሮው ኢሬቻ በዓል መስከረም 23 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚከበር መገለጹ ይታወቃል።

በዚህም የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ  አባገዳዎችና ወጣቶች  በዓሉን  በሠላም ማክበር በሚቻልበት ጉዳይ ላይ መክረዋል።

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍቃዱ ካሳሁን ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ኢሬቻም እንደ መስቀል በዓል  በሰላም እንዲከበር  አባቶችና ወጣቶች የድርሻቸውን እንዲወጡ በመድረኩ ውይይት ተደርጓል።

"በእዚህም አባገዳዎቹ በሚያዙት መሰረት በዓሉ ስርዓቱን  በጠበቀ  መልኩ  በሠላም እንዲከበር ወጣቶች የድርሻቸውን እንዲወጡ ተልዕኮ ይወስዳሉ" ብለዋል።

ወጣቱን ከአባገዳዎቹ ጋር ማወያየት ያስፈለገውም “አባገዳዎቹ ለወጣቱ ሠላምን እንዲያውጁ ፣ አብሮነትን  እንዲሰብኩ  ለማስቻል  ነው”  ብለዋል  አቶ ፍቃዱ፡፡

ይህም አባገዳዎቹ ወጣቱ ለሠላም ዘብ እንዲቆም እንዲመክሩና እንዲገስጹም ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ነው ያስረዱት።  

አቶ ፍቃዱ እንዳሉት በዕለቱም ወጣቶቹ በዓሉን  ለማክበር ከሌላ አካባቢ  ለሚመጡ የበዓሉ ታዳሚዎች አቀባበል ሲያደርጉ፤ አባገዳዎቹ ደግሞ ስርዓቱ በሚጠይቀው መንገድ ወጣቶቹን የመምራት ሚና ይኖራቸዋል።

አባገዳ በቀለ ሄርጳሳ እንዳሉት በዓሉ የኦሮሞ ህዝብ ጥንካሬና መከባበር  መገለጫ  በመሆኑ ሁሉም ወጣት ከአባገዳዎች  በሚሰጠው ትዕዛዝ  መሠረት  እንዲያከብር አሳስበዋል።

“ኢሬቻን ለትውልድ ለማስተላለፍ አልተኛንም” ያሉት አባገዳ በቀለ፤  "ዘላቂነት እንዲኖረውም ወጣቱ ምክራችንን መስማት አለበት" ብለዋል።

በቅርቡ በተከበረው የመስቀል ደመራ በዓል የታየው ሰላም በመጪው ቅዳሜ በአዲስ አበባ በሚከበረው የኢሬቻ በዓል ላይም እንዲደገም  የበኩላቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።

ወጣት ጫልቱ ለማ በበኩሏ ከአባገዳዎችና ከመንግስት አካላት በሚሰጥ አቅጣጫ መሰረት የአባቶችን አርአያ በመከተል ሠላም፣ አብሮነትና መከባበርን በኢሬቻ ዕውን ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ተናግራለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም