የኢሬቻ በዓል ኮቪድ-19ን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሊከበር ይገባል

52

አዲስ አበባ መስከረም 19/2013 (ኢዜአ) የኢሬቻ በዓል የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሊከበር እንደሚገባ ተገለጸ።
የካ ክፍለ ከተማ የበዓሉን አከባበር አስመልክቶ ከወጣቶች ጋር ተወያይቷል።

የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል ከወትሮው በተለየ መልኩ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ታሳቢ በማድረግ ሊከበር እንደሚገባ በውይይቱ ተገልጿል።

የኢሬቻ በዓል አንድነትንና የብሔር ብሔረሰቦችን መልካም ግንኙነት የሚያጠናክር ነው።

ከበዓሉ የሚገኘው ገቢም ለአገሪቷ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ በውይይቱ ላይ ተገልጿል።

ይሁንና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ ኢሬቻ ብቻ ሳይሆን በርካታ ሕዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላትን እንደ ቀደመው ጊዜ ማክበር አልተቻለም።

የየካ ክፍለ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደመላሽ ጎሳ ወጣቶች ራሳቸውንና  ኅብረተሰቡንም ከወረርሽኙ በመከላከል በዓሉን እንዲያከብሩ ለማድረግ ውይይቱ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በዓሉ የቀደሙ በዓላት በተከበሩበትና አባ ገዳዎች በሚያስቀምጡት አቅጣጫ መሰረት ኮቪድ-19ን ባገናዘበ ሁኔታ እንደ ሚከበርም ገልጸዋል።

በውይይቱ የተሳተፉት ወጣት ሹሙ መስቀሌና ካሳሁን አሰፋ በዓሉ ሠላምን በሚያውኩ አካላት እንዳይደናቀፍ ከፀጥታ አካላት ጋር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የበዓሉን ማክበሪያ ስፍራ በማፅዳት፣ በደም ልገሳና የተቸገሩን በመርዳት እንደሚያከብሩት በመግለፅ ወጣቶች ለዚህ እንዲተባበሩ ጠይቀዋል።

ከስሜታዊነት በመራቅ በተረጋጋ መንገድ በዓሉን ሊያከብሩ ይገባል ብለዋል።

ወጣቶች የአባ ገዳዎችን ምክር እንዲቀበሉ፤ ኅብረተሰቡም የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ታሳቢ በማድረግ በዓሉን በየአካባቢው እንደሚያከብርም ነው የጠየቁት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም