መገናኛ ብዙሃን ባገኙት ነጻነት ልክ የህግ የበላይነትን አለማክበራቸው በመረጃ ነፃነት መብት ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው

136

አዲስ አበባ መስከረም 19/2013 (ኢዜአ) መገናኛ ብዙሃን በተሰጣቸው ነጻነት ልክ የህግ የበላይነትን ማክበር አለመቻላቸው የመረጃ ነፃነት መብት ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን የኢትዮጵያ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ገለፀ።

ወቅታዊ መረጃዎች በሚመለከታቸው አካላት ተደራሽ አለመሆን ህብረተሰቡ ለማህበራዊ ሚዲያና ለጥላቻ ንግግር እንዲያዘነብል ማድረጉንም አመልክቷል።

የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በዓለም ለ5ኛ ጊዜ ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ3ኛ ጊዜ በመጪው ሐሙስ የሚከበረውን የመረጃ ነፃነት ቀን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የተቋሙ ዋና ዕንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ እንዳሉት የመረጃ ነፃነት ሃሳብን የመግለፅ መብት አካል ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በኢትዮጵያ ህጋዊ እውቅና ያገኘ ነው።

የህግ ማዕቀፎች ዝግጅት፣ የክትትልና ድጋፍ እንዲሁም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የመረጃ ነፃነትን በተመለከተ የሚያከናውናቸው ዋና ዋና ተግባራት እንደሆኑም ተናግረዋል።

በህገመንግስቱና በአዋጅ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽና ለመረጃ ነፃነት መብት እውቅና መሰጠቱ፣ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ አንፃራዊ በሆነ መልኩ ሃሳብን በነፃነት መግለጽ መቻሉ፣ አማራጭ መገናኛ ብዙሃን መኖራቸውና  መረጃ ተደራሽ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ በአገሪቱ ለመረጃ ነፃነት ተግባራዊነት ምቹ ሁኔታዎች መሆናቸውን አመልክተዋል።

ዶክተር እንዳለ እንዳሉት ያልሰለጠነና ያልዘመነ ፖለቲካ መኖር እንዲሁም መረጃን በማይሰጡ አካላት ተጠያቂነት ላይ ያለው የህግ ክፍተት ለመረጃ ነፃነት አዋጅ አተገባበር ተግዳሮት ሆነዋል።

ተቋማት በየደረጃው ላሉ ምክር ቤቶች ሪፖርት ሲያቀርቡ የመረጃ ነፃነት አዋጅን አተገባበር ጨምረው ማቅረብ እንዳለባቸው በአዋጁ ቢቀመጥም ምክር ቤቶች ይህን አለመጠየቃቸውም ከተግዳሮቶቹ መካከል መሆኑን ተናግረዋል።

"አስፈፃሚ አካላት ወቅታዊ መረጃን ለመገናኛ ብዙሃን ተደራሽ ባለማድረጋቸው ህብረተሰቡ ለማህበራዊ ሚዲያና ጥላቻ ንግግር ተጋላጭ ሆኗል" ነው ያሉት ዶክተር እንዳለ።

መገናኛ ብዙሃን በተሰጣቸው ነፃነት ልክ የህግ የበላይነትን ማክበር እንዳለባቸው በመገንዘብ እየሰሩ አለመሆኑም ለመረጃ ነጻነት መብት ተግዳሮት መሆኑን ዶክተር እንዳለ አንስተዋል።

በ74ተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በየዓመቱ እንዲከበር በተላለፈ ውሳኔ መሰረት መስከረም 28 የመረጃ ነፃነት ቀን ሆኖ እንዲከበር ተወስኗል።

የዘንድሮው የመረጃ ነፃነት ቀን "የመረጃ ነፃነት ለህይወት ደህንነት፣ ለታማኝነት እና ለብሩህ ተስፋ" በሚል መሪ ሃሳብ በአገራችን መስከረም 21 ቀን በአዳማ ከተማ በፓናል ውይይት እንደሚከበር ተገልጿል።

በመድረኩም የኮቪድ-19 እና የመረጃ ነፃነት አተገባበር በሚሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት ይደረጋል ተብሏል።
በመድረኩም የተለያዩ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የግልና የመንግስት መገናኛ ብዙሃን አመራሮችና የሚመለከታቸው አካላት እንደሚሳተፉም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም