ለሕዳሴ ግድብ የሚደረገው የዲፕሎማሲ ሥራ በተደራጀ መንገድ ይቀጥላል -- አምባሳደሮች

61

አዲስ አበባ መስከረም 19/2013 (ኢዜአ) የሕዳሴው ግድብ እስኪጠናቀቅ ድረስ የኢትዮጵያን ምክንያታዊ አቋም ለዓለም የማስረዳትና የዲያስፖራውን ተሳትፎ የማጠናከር ሥራ በተደራጀ መንገድ እንደሚቀጥል በተለያዩ አገራት ያሉ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ገለጹ።

በአሜሪካ የሚኒሶታና ሚድዌስት ቆንስላ ጀነራል አምባሳደር አብዱልአዚዝ መሀመድ ለኢዜአ እንዳሉት ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕጋዊ መሠረት ይዛ ግድቡን እየገነባች ስለመሆኑ የማስረዳት ሥራ እየተከናወነ ነው።

በእዚህም ግድቡ እየተገነባ ያለው ፍትሐዊ የውኃ ተጠቃሚነትና በጋራ የመልማት መርህን በመከተል በመሆኑ በዓባይ ተፋሰስ አገሮች ላይ የተጠቃሚነት ጉዳት እንደማያሳደር በማስረዳት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በተሠራው የዲፕሎማሲ ሥራ የዓባይ ውኃን 86 በመቶ የምታመነጨው ኢትዮጵያ ግድቡን እየሠራች የምትገኘው ሕዝቦቿን ከድህነት ለማውጣት መሆኑ ግንዛቤ እየተያዘ መምጣቱንም አንስተዋል።

አምባሳደር አብዱልአዚዝ እንዳሉት የግድቡ የመጀመሪያ ውኃ ሙሌት ከተጠናቀቀ በኋላ ዲያስፖራው በዕውቀትና በገንዘብ ለመደገፍ ከፍተኛ መነሳሳት አሳይቷል።

በቀጣይም ፕሮጀክቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ስለግድቡ ዘርፈ ብዙ ጥቅም የማስረዳት፣ የማሳመንና ዲያስፖራው ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል የማስተባበሩ ሥራ በስፋት እንደሚሠራ አመልክተዋል።

በሳዑዲ ዐረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አብዱልአዚዝ አህመድ በበኩላቸው የኢትዮጵያን አቋም ለዓረቡ ዓለም ለማስረዳት የዲፕሎማሲ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

መገናኛ ብዙሃንና ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም በዐረብኛ ቋንቋ የኢትዮጵያን አቋም ማስረዳት አንዱ ተግባር መሆኑንም ተናግረዋል።

እንደ አምባሳደሩ ገለጻ ኢትዮጵያዊያን የዐረብኛ ቋንቋን በመጠቀም ለመሪዎች፣ ለምሁራንና ዲፕሎማቶች የአገራቸውን አቋም ለማስረዳት የሚያከናውኑት ሥራ በተደራጀ መንገድ ይቀጥላል።  

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው እንደተናገሩት የኢትዮጵያን አቋም ለዓለም ማስረዳት ሁሉም የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች በየዕለቱ ከሚያከናውኗቸው ሥራዎች ውስጥ አንዱ ነው።

በዚህም ኢትዮጵያ በሕዳሴው ግድብ እያራመደች ያለውን አቋም የሚረዱ አገሮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።

ከኢትዮጵያ ሕዝብ ከ60 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው መብራት ባለማግኘቱ ተማሪዎች በኩራዝ ለማጥናት እንደሚገደዱ፣ እናቶች ውኃ ፍለጋ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን እንደሚያቋርጡ በተጨባጭ ያለውን ችግር ዓለም እንዲረዳ እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።

የግድቡ የመጀመሪያ ውኃ ሙሌት ቢጠናቀቅም በቀጣይ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ እንደሚጠይቅም አምባሳደር ሬድዋን ተናግረዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያን በተለያዩ የዓለም አገሮች የወከሉ ዲፕሎማቶች የአገራቸውን ትክክለኛ አቋም ማስረዳት የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ሆኖ መቀጠል አለበት።

ዲያስፖራው ለሕዳሴ ግድብ በገንዘብ፣ በዕውቀትና የኢትዮጵያን አቋም በማስረዳት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ሚኒስትር ዴኤታው ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም