የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ነገ የሚያከብረውን በዓል አስመልክቶ የፓናል ውይይት እያካሄደ ነው

82

አዲስ አበባ መስከረም 19/2013 (ኢዜአ) የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን " ከራስ በላይ ለሀገርና ለህዝብ! " በሚል መሪ ቃል ነገ የሚያከብረውን በዓል አስመልክቶ በሸራተን አዲስ ሆቴል የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።

በፓናል ውይይቱ ላይ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እና ሚኒስትሮችን ጨምሮ  የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ጥሪ የተደረገላቸው አምባሳደሮችና የፖሊስ ሠራዊት አባላት ተገኝተዋል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው በዚህ ወቅት እንዳሉት የፖሊስ ተልዕኮ ከጊዜ ወደጊዜ እየከበደና በውስጥም በውጭም በርካታ ፈተናዎች እየገጠሙት መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከአገራዊ ለውጡ ጋር በተያያዘ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች እየገጠሙት መሆናቸውን ጠቅሰው፣ እነዚህን ችግሮች መፍታት በሚያስችል መልኩ ተቋሙን የመለወጥ ሥራ በጥናት እየተካሄደ መሆኑንና በአሁኑ ወቅትም የለውጥ ሥራው መጀመሩን አመልክተዋል።

በዚህም በአደረጃጀት፣ በሰው ኃይል፣ በግብዐት አቅርቦት፣ በቴክኖሎጂና በመሳሰሉት የነበሩበት ችግሮች እየተፈቱ ተጨባጭ ለውጦች እየመጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎችን ለማስቀጠልና የህግ የበላይነት እንዲከበር የበለጠ እንደሚሰራም ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው አረጋግጠዋል።

የክልል መንግስታት ለዚህ የሚመጥን የሰው ኃይል ግንባታ ላይ የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

በመድረኩ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ አስካሁን ድረስ የተጓዘበትን ሂደት የሚያሳይ ዶክመንተሪ ፊልም ለታዳሚዎች ቀርቧል።

በቀጣይም የመወያያ ሰነድ ቀርቦ በተሳታፊዎች ውይይት እንደሚደረግበትና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንም ለፖሊስ መልዕክትና የሥራ መመሪያ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም