በድሬዳዋ 358 የጋራ ቤቶችን ለተጠቃሚ ለማስተላለፍ እየተሰራ ነው

45

ድሬዳዋ መስከረም 19/2013 (ኢዜአ)- በደሬዳዋ ከተማ በ169 ሚሊዮን ብር  በግንባታ ላይ ያሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በቅረቡ ተጠናቀው ለተጠቃሚ እንደሚተላለፉ የአስተዳደርሩ የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በጽህፈት ቤቱ የኮንስትራክሽን አስተዳደር ግንባታ ጥራት ቁጥጥር መመሪያ ኃላፊ አቶ ሶፎንያስ አድማሱ ለኢዜአ እንደገለጹት ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመሩ የ358 የጋራ ቤቶች ግንባታ ስራ 75 በመቶ ተጠናቋል ።

በግንባታ ላይ ያሉት ቤቶች ባለ 10/90ና  ባለ 20/80  መሆናቸውን ተናግረዋል ።

የቤቶቹን ግንባታ  በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ለተጠቃሚ ለማስተላለፍ አየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

"በቤቶቹ ግንባታ በ40 የኮንስትራክሽንና አነስተኛ ሥራዎች ማህበራት ለተደራጁ ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል" ብለዋል።

የጽህፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፈለቀ ፈረጃ በግንባታ ላይ ባሉት  ቤቶች  ለመግባት ከ16 ሺህ በላይ ሰዎች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

የቤት ባለቤት ለመሆን ከተመዘገቡና ገንዘባቸውን ከቆጠቡ ሠራተኞች መካከል ወይዘሮ አይናለም ጎንጤ የደሞዛቸውን ግማሽ ያህል ለግለሰብ ቤት ኪራይ እንደሚያውሉት ተናግረዋል፡፡

"በግለሰብ ቤት ልጆቾች ይዞ መኖር ከባድ ነው፤ በስራ ላይም ከፍተኛ ተፅዕኖ ይፈጥራል" ብለዋል፡፡

የቤቶቹ ግንባታ ተጠናቆ በእጣ እስኪከፋፈል በጉጉት እየተጠባበቁ መሆናቸውን አስታወቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም