በአማራ ክልል በመስሪያ ቤቶች የአሰራር ክፍተት በግዥ ስርዓቱ ላይ ችግር መፍጠሩ ተገለጸ

37

ባህር ዳር መስከረም 19/2013 (ኢዜአ) መስሪያ ቤቶች የአሰራር ክፍተት በግዥ ስርዓቱ ላይ ችግር መፍጠሩን የአማራ ክልል የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት አስታወቀ።

የአገልግሎቱ የመንግስት ግዥ ዳይሬክተር አቶ ይታያል ገበየሁ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ

አግልግሎቱ ከተቋቋመ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ ለሚገኙ ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የተለያዩ ግዢዎችን እየፈጸመ ይገኛል ብለዋል።

በአገልግሎቱ የሚገዙ ግዢዎች ልዩና ውስን መሆናቸውን ጠቅሰው ፤ የተሽከርካሪ ጎማዎች፣ የቢሮ መገልገያ እቃዎችና መሳሪያዎች፣ ፎቶ ኮፒ፣ ፋክስ፣ የፕሪንተር ቀለሞች፣ የተሽከርካሪ ጥገናና የመድን ዋስትና ግዥ እንደሚፈጸሙ ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም የክልሉ የጸጥታ አካላት የደንብ ልብስ፣ የኮንስትራክሽን መሳሪያዎችንና ልዩ ልዩ ተሽከርካሪዎችን ግዥ እንደሚገኝባቸውም አስረድተዋል።

በ2012 የበጀት ዓመት ስድስት ጨረታዎች በማውጣት 540 ሚሊዮን ብር ወጭ ተደርጎ የተለያዩ ግዢዎች መፈፀማቸውንም አስታውቀዋል።

ይህም ከጥራትና ከፍጥነት አኳያ ከባለፉት ዓመታት ጋር ሲወዳደር የተሻለ የነበረ ቢሆንም ተቋማት የሚገዟቸውን የግዥ ዓይነቶች በጥራት ዘርዝሮ በማቅረብ በኩል ክፍተቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።

ክፍተቶቹም የተቋሙ አመራር ይሁንታ አግኝቶና ፀድቆ አለመዘጋጀት፣ እንዲፈጸምላቸው የሚፈልጉ ተቋማት የግዥ እቅዳቸውን ለአንድ ባለሙያ ኃላፊነቱን በመስጠት የሚመለከታቸው አመራሮች የጋራ አድርገው ተወያይተው አለማቅረባቸውን ጠቅሰዋል።

በዚህም  በግዥ ስርዓቱ ላይ ተግዳሮት እንዲሆን አድርጎታል ብለዋል።

በክልሉ መንግስት ከሚመደብ በጀት ከ60 እስከ 70 በመቶው ለግዥ አገልግሎት የሚውል መሆኑን ያመለከቱት  አቶ ይታያል ይህንን ተገንዝቦ የግዥ ዓይነቶችን በጥራትና ፍጥነት ዘርዝሮ በማቅረብ ሊተባበሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የተያዘው  በጀት ዓመት የተቋማት የግዥ ስራዎች መጀመራቸውን ገልጸው፤ እስካሁን 161 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው የግዥ ዓይነቶች ግዥ መፈፀሙን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም