ሕዝባዊ በዓላት በሠላማዊ መንገድ እንዲከበሩ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል

58

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19/2013 ( ኢዜአ) ሕዝባዊ የአደባባይ በዓላት ያለ ምንም ችግር በሠላም እንዲከበሩ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ አሳሰቡ።

በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊው ዶክተር ቢቂላ እነዚህ በዓላት የኢትዮጵያዊያን ሁለንተናዊ መገለጫዎች ናቸው ብለዋል።

ሕዝባዊ በዓላት የአብሮነትና የአገሪቷ ሕዝቦች ልዩ መገለጫዎች፤ ከክብረ በዓልም በላይ የሆኑ ልዩ ክንውኖች ናቸው ነው ያሉት።

በዓላቱ የሕዝቦች ተቻችሎ የመኖር እሴት የሚገለጽባቸው፣ አንዱ ሌላውን የሚያውቅበትና የሚያከብርበትን ክስተት የሚፈጥሩ ሁናቶች መሆናቸውንም አብራርተዋል።

ዶክተር ቢቂላ ሕዝባዊ በዓላቱን "ኢትዮጵያዊያን ብዝሃነትን በጠበቀ መልኩ በጋራ የሚደሰቱባቸው ቀናት ናቸው" ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

በተለይ ደግሞ መስቀልና ኢሬቻ ከሌሎች በዓላት ልዩ የሚያደርጋቸው ገጽታ እንዳላቸው ነው የተናገሩት።

ለዚህም ሁለቱ በዓላት በተከታታይ የሚከበሩ፣ አንዱ ለሌላው ነጸብራቅ መሆኑና በበርካታ ሕዝብ መከበራቸው መሆናቸውን ነው የጠቀሱት።

በመሆኑም እነዚህ የሕዝብ መገለጫ በዓላት በሠላም እንዲከበሩ ሁሉም ዜጋ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት ነው ያሉት ዶክተር ቢቂላ።

የሰውን ልጅና ኢትዮጵያዊያንን የሚያከብር ለበዓላቱ በሠላም መጠናቀቅ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

ከሁሉም በላይ ወጣቶች ሃሳባቸውን ለመግለጽ ሠላማዊውን መንገድ መከተል እንዳለባቸውም መክረዋል።

ጥያቄዎችን በሰለጠነና በሰከነ መንገድ ማቅረቡ የተሻለ ነው ይላሉ ዶክተር ቢቂላ።

በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ትልቅ ስፍራ ያለው የኢሬቻ በዓል በመጪው ቅዳሜና እሁድ ይከበራል።

ዶክተር ቢቂላም የኢሬቻን በዓል ለሚያከብሩ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም