ከ20 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሊተላለፉ ነው ---ከተማ አስተዳደሩ

72

አዲስ አበባ  መስከረም 18/2012 ( ኢዜአ) ከመስከረም 21 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ከ20 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች የጋራ መኖሪያ ቤቶችን እንደሚያስተላለፍ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

ከተማ አስተዳሩ ከልማት ተነሺ አርሶ አደር ተወካዮችና መረጃ ማጥራት ሥራ ሲያከናወኑ ከነበሩ የክፍለ ከተማና ወረዳ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ዛሬ ተወያይቷል፡፡

በውይይቱም በከተማ አስተዳደር ደረጃ በአዲስ አበባ መሬት አስተዳደር ኮሚሽን ሲከናውኑ የነበሩ ሥራዎችን የተመለከተ ሪፖርት ቀርቧል፡፡

በእዚህም የልማት ተነሺ ለሆኑ አርሶ አደሮች የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በፍጥነት ለማስተላለፍ የመረጃ ማጥራት ሥራ ሲከናወን መቆየቱ ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንዳሉት ምንም አይነት ጥያቄ ያልተነሳባቸው 20 ሺህ 792 የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ከመስከረም 21 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ማስተላለፍ ይጀመራል፡፡

በጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ የመሰረተ ልማቶችን ለማሟላት በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ ሥራ መጀመሩንም አመልክተዋል፡፡

በየትኛውም የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ መረጃ አለኝ የሚል አካል ካለ ህጉ ስለሚፈቅድ ማቅረብ እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡

"ከወሰንና ሌሎች ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ችግሮች ያሉባቸውን ቦታዎችም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት በማድረግ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹን የማስተላለፍ ሥራው በፍጥነት ይካሄዳል" ብለዋል፡፡

ከሁሉም የመዲናዋ ነዋሪዎች ጋር መረዳዳትና መተሳሰብ እንደሚያስፈልግ ያስገነዘቡት ወይዘሮ አዳነች፣ "በጋራ መኖሪያ ቤቶችና በሌሎች ተያያዥ ጥቃቅን ጉዳዮች ሊከፋፍሉን የሚፈልጉትን መዋጋት ይገባል" ብለዋል፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር ዓባይ በበኩላቸው፣ እስካሁን የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ለልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ሳይተላለፉ የቀሩት ቤቶቹ ለሚገባው አካል እንዲተላለፉ በማሰብ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለልማት ተነሺዎች ቤቶችን ለማስተላለፍ ሲሰራ መቆየቱን የገለጹት ደግሞ የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ አለሙ ናቸው፡:

የጋራ መኖሪያ ቤቶች የግንባታ ሥራ መጓተት አርሶ አደሮቹን ለከፋ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት ሲዳርግ መቆየቱ በመድረኩ ተነስቷል፡፡

አሁን በሚሰጡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ያልታቀፉ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን ከተማ አስተዳደሩ ቀጣይ በሚያከናውናቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ተጠቃሚ ለማድረግ ይሰራል ተብሏል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች ቤቶቹ ለልማት ተነሺ አርሶ አደሮች የሚተላለፉበት ጊዜ አጭር እንደሆነና ሌሎች በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ያሉ የመሰረተ ልማት ጉዳዮች እንዲሟሉ ጥያቄዎችን አቅርበው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት በምግብ ኮምፕሌክስ ማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩት ባለሃብት አቶ ኑሩሱልጣን መሃመድ የከተማ አስተዳደሩን "ለአንድ ተማሪ አንድ ጫማ" ጥሪ በመቀበል ለከተማ አስተዳደሩ የ5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም