ሚኒስቴሩ አረጋዊያንን በዘላቂነት ለማገዝ የሚያስችል አሰራር ለመተግበር እየተዘጋጀ ነው

49

  አዲስ አበባ  መስከረም 18/2012 ( ኢዜአ) አረጋዊያንን በዘላቂነት ለማገዝ የሚረዳ የማህበራዊ ጥበቃ ፈንድና ብሔራዊ ምክር ቤት ሊያቋቁም መሆኑን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ይህ የተገለጸው በአገር አቀፍ ደረጃ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የአረጋዊያን ቀን አስመልክቶ ዛሬ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።

የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስተሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በእዚህ ወቅት እንዳሉት አረጋዊያን በፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸው ፋይዳ የጎላ ነው።

"በተለይም ትውልድን በመልካም እሴቶች በማነጽና የአገር እድገትን በእውቀትና በተሞክሮ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ የላቀ ነው" ብለዋል።

ይሁን እንጂ ለአረጋዊያን መሰጠት ያለበትን ያክል ክብርና እውቅና በመስጠት በኩል እንደአገር ሰፊ ክፍተቶች መኖራቸውን ሚኒስትሯ አንስተዋል።

እንደእሳቸው ገለጻ በአገሪቱ ቁጥራቸው ከ6 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ አረጋዊያን ያሉ ሲሆን አብዛኞቹም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚኖሩና ድጋፍን የሚሹ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት 296 ሺህ 643 አረጋዊያን በሴፍትኔት መረሃግብር እየተደገፉ ቢሆንም በሚፈለገው መልኩ ተደራሽ ማድረግ አለመቻሉንም አመልክተዋል።

በዚህም አረጋዊያንን በስፋትና በዘላቂነት ለማገዝ ሚኒስቴሩ የማህበራዊ ጥበቃ ፈንድና የማህበራዊ ጥበቃ ምክር ቤትን የማቋቋም ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ሚኒስትሯ አክለውም የዓለም የአረጋዊያን ቀን ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በተለያዩ ኩነቶች ከመስከረም 21 ቀን ጀምሮ ለሁለት ቀናት እንደሚከበር አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ አረጋዊያንና ጡረተኞች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ክፍሉ በበኩላቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመንግስትና በማህበረሰቡ ዘንድ የተስተዋለው አረጋዊያንን የማክበርና የማገዝ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በተለይም በኮቪድ-19 ሳቢያ ለችግር የተጋለጡ አረጋዊያንን በመለየት እየተደረገ ያለው የማዕድ ማጋራት፣ የቤት እድሳትና ሌሎች ድጋፎች  ምስጋናቸውን ችረዋል።

በዓሉ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ አረጋዊያን ተሳትፏቸውን እንዲያጎለብቱና ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል የሚል እምነት እንዳላቸውም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

በተለይም በሰላምና ደህንነት ዙሪያ በመላ አገሪቱ የተለያዩ ሥራዎች የሚከናወኑበትና ከተተኪው ትውልድ ጋር የእውቀት ቅብብሎሽ የሚደረግበት መሆኑንም አመልክተዋል።

ዓለም አቀፍ የአረጋዊያን ቀን በዓል ''ወቅታዊና ተግባራዊ ምላሽ ለአረጋዊያን'' በሚል መሪ ሃሳብ በኢትዮጵያ ለ29ኛ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ30ኛ ጊዜ በመጪው ሐሙስ እንደሚከበር ታውቋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም