ሀብታቸውን ያላስመዘገቡ አመራሮች በገንዘብ ቅጣት ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ሊደረግ ነው

82

  አዲስ አበባ  መስከረም 18/2012 ( ኢዜአ) ሀብታቸውን ያላስመዘገቡ የክፍለ ከተማና የወረዳ አመራሮች በገንዘብ ቅጣት ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ሊደረግ መሆኑን የፌደራል የሥነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።

የፌደራል የሥነ ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከአሥሩም ክፍለ ከተሞች ከተውጣጡ አመራሮች ጋር በሀብት ምዝገባ ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።

በዚህም በተቀመጠው መደበኛ የሀብት ማስመዝገቢያ ጊዜ ሃብታቸውን ያላስመዘገቡ የወረዳና የክፍለ ከተማ አመራሮች በገንዘብ ቅጣት በአምስት ቀናት ውስጥ ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ የጊዜ ገደብ መቀመጡ ተገልጿል። 

ምክትል ኮሚሽነሩ አቶ ወዶ አጦ እንደገለጹት ከአሥሩ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈፃሚዎች መካከል በጊዜ ገደቡ ሀብታቸውን ያስመዘገቡት የቦሌ፣ የአራዳ እና የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚዎች ብቻ ናቸው።

በመሆኑም "ሀብታቸውን ያላስመዘገቡ የክፍለ ከተማና የወረዳ አመራሮች ከዛሬ መስከረም18 እስከ 22 ቀን 2013 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በተሻሻለው የሃብት ማሳወቅ እና ምዝገባ አፈፃፀም መመሪያ ቁጥር 1/2013 መሠረት ለኮሚሽኑ የእንድ ሺህ ብር ቅጣት በመክፈል የሀብት ማስመዝገብ ግዴታቸውን እንዲወጡ ይደረጋል" ብለዋል። 


በኮሚሽኑ የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መስፍን በላይነህ በበኩላቸው አመራሮቹ በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ሀብታቸውን በማስመዝገብ ግዴታቸውን የማይወጡ ከሆነ ኮሚሽኑ በሙስና ወንጀል እንዲጠየቁ ጉዳዩን አግባብነት ላለው የምርመራ አካል ያስተላልፋል።

በውይይቱ ላይ 30 የክፍለ ከተማ አመራሮች የተሳተፉ ሲሆን በጉዳዩ ላይ የተሻለ ግንዛቤ ይዞ ሙስናን በጋራ መከላከል እንዲህ አይነት መድረኮች በቀጣይም ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም